“የህግ የበላይነት ሲባል…..”

በኃይለማርያም ይርጋ
መግቢያ

የኛ ሰው ፀብ የለሽ በዳቦ የሆነ አምባጓሮ ሲገጥመው፣ ንብረቱ ሲደፈር፣ ቃል አባይ በሆነ ሰው ሲከዳ፣ በመንግስት አካላት ሆነ በግለሰብ መብትና ጥቅሙ ያለ አግባብ ሲገፈፍ ፍትህ በ’ጄ ብሎ መብቱን በሃይል ከማስከበር ይልቅ በህግ አምላክ& ብሎ እማኝ ቆጥሮ ጉዳዩን ወደ ባህላዊ ፍርድ ሰጪ ወይም ህግ አስከባሪ አካል ወይም መደበኛ ፍርድ ቤት ይዞ በመሄድ መብቱን የማስከበር አኩሪ ባህል አለው። ይህ ባህል የሁሉም የክልላችን ህዝቦች መገለጫ ነው። ከመደበኛው የፍትህ አስተዳደር በተጨማሪ የሲዳማው አቦ ወንሾ ፣ የጉራጌው ጆካ፣ የየሙ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ወ.ዘ.ተ በክልላችን ከሚገኙ ርዕትእንና ህገ ልቦናን መሰረት ያደረጉ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ናቸው። ይህ የሚያሳየው የሃገራችን ዜጎች ምን ያህል ለህግ ተገዥ መሆናቸውን ነው። ሆኖም ግን በሃገራችን የተፈጠረውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ አንዳንድ የሃገራችን ክፍሎች ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት በመንገሱ መሰረታዊ የግለሰብና የቡድን መብቶች ሲጣሱ ይስተዋላል። በመሆኑም ፓለቲከኞች፣ ኢንቨስተሮች፣ ነጋዴዎች፣ ሙሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት &የህግ የበላይነት ያስከብር በማለት በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን መልእክት ሲያስተላልፉ ማየት የተለመደ ሆኗል። በተጨማሪም የመንግስት ባለስልጣናት በአንድ ጉዳይ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሆን ሲገልፁ በሌላ በኩል ደግሞ ተፎካካሪዎችና ሊሂቃን ውሳኔው የህግ የበላይነትን የተቃረነ መሆኑን በመግለፅ ተፈፃሚነቱን ሲቃወሙ ይስተዋላል። ለመሆኑ ይህ አሳሳቢ የሆነው የህግ የበላይነት፤ ምን ማለት ነው? መስፈርቶቹስ? ጠቀሜታዎቹስ የሚሉትን ጉዳዮች ከሃገራችን ህጎች እና አለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው መለኪያዎች አንፃር እናያለን። አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባው ጉዳይ የህግ የበላይነት በፅንስ ሃሳብ ደረጃ በህግ ሙሁራን ዘንድ ክርክር እየተደረገበት ያለ ያልተቋጨና ብዙ መፅሃፍች የተፃፈበት ግዙፍ ሃሳብ መሆኑን ነው። በመሆኑም በዚህ የግንዛቤ መስጫ ፅሁፍ የፅንሰ ሃሳቡን አንኳር ነጥቦች ብቻ የምንመለከት ይሆናል።

የሕግ የበላይነት ትርጉም

በኢፌድሪ ሕገመንግስት መግቢያ ላይ “ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን…..በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ አንድ ፓለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት..” በሚል የሕግ የበላይነት ለሃገራችን ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሆኖም ግን የሕግ የበላይነት የሚለው ቃል በህገ መንግስቱም ሆነ በሌሎች አለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶች ቢጠቀስም ስምምነት ላይ የተደረሰበት አንዳች ትርጉም ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡ ከመዝገበ ቃላት ትርጉም ይልቅ የተሟላ ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ ዊሊያም ጋርድነር የተባለ የሕግ ሙሁር “THE HISTORY AND ELEMENTS OF THE RULE OF LAW” በተሰኘው መፅሀፍ ላይ ያስቀመጠውን ትርጉም እና የተባበሩት መንግስታት ድርግጅት ዋና ዳይሬክተር በ2014 እኤአ ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፓርት ላይ ለህግ የባላይነት የተሰጠውን ትርጉም እናያለን፡፡

ዊሊያም የህግ በላይነትን አጭር እና ግልፅ በሆነ አገላለፅ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል ፤

“የሕግ የበላይነት ማለት የመንግስት አካላት፣ ባለስልጣናት(ሰራተኛውን ጭምሮ) እና ዜጎች በሕግ ጥላ ስር ሲወሰኑና ሲያክብሩ ነው “ የሚል ነው፡፡

በአንድ ማህበረሰብ የመንግስት ባለስልጣናትና ዜጎች የእለት- ተለት ስራቸውን የሚፈፅሙት በህግ ጥላ ስር ሆነው ህግን በማክበር ከሆነ በህግ የበላይነት የሚመራ ማህበረሰብ ይባላል፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ የተገለፀው ህግ ለውጥን ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ በጠቅላላ አገላለፅ የተረቀቀና በቀላሉ የሚረዱት፣ ተደራሽ የሆነ፣ ሊፈፀም የሚችል፣ ሁሉም በህግ ፊት እኩል የሆነበት እንዲሁም ህጉ በማይከበርበት ወቅት የማስፈፀሚያ ስርዓትና ተቋማት ሊኖረው ይገባል ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ የሕግ የበላይነት ሊኖር አይችልም ይላል ዊሊያም፡፡ ለምሳሌ ህጉን የማስፈፀሚያ ስርዓት እና ተቋማት ከሌሉ ወይም ስራቸውን በአግባቡ ካልተወጡ የሕግ የበላይነት እንደሌለ ይቆጠራል፤ ባለስልጣኑም ሆነ ዜጋው ልጓም እንደሌለው ፈረስ እንዳሻው ይፈነጫል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዊሊያም ከሰጠው ትርጉም በሰፋ መልኩ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:-

“ የሕግ የበላይነት የአስተዳደር መርህ ሲሆን ሁሉም ሰው፣ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት በግልፅ በፀደቀ፣ ያለአድሎ በእኩል በሚፈፀም፣ በገለልተኛ ፍርድ ቤት በሚተረጎም እና ከአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነዶች ጋር በተጣጣመ ህግ ተጠያቂ መሆንን የሚያመለክት ሲሆን ተጠያቂነትን፣ ርትዕን፣ ተገማችነትን፣ የስልጣን ክፍፍልን፣ በውሳኔ ሰጪነት ተሳታፊነትን፣ የዘፈቀደ አሰራርን ለማስወገድ እና የህግና የሥነ ስርዓት ግልፀኝነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሂደትና ጥረት ይጨምራል” በማለት ይተረጉመዋል፡፡

ፅንሰ ሃሳቡን የሚያጠኑ የሕግ ሊሂቃኖች ከላይ ከተመለከቱት ትርጉሞች አንፃር እይታቸው በሁለት የሚከፈል ሲሆን ሕጋዊነትን መሰረት ያደረገ ዝቀተኛው (formal or procedural conception) እይታ እና መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያካተተ (substantive conception) የህግ የበላይነት በሚል ይከፈላል፡፡ ህጋዊነትን መሰረት ያደረገው ዝቅተኛው የሕግ የበላይነት እይታ ዊሊያም ከሰጠው ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ህግ መሰረታዊ የአስተዳደር መሳሪያ ሲሆን አግባብ ባለው ባለስልጣን ይመነጫል፣ ግልፅ፣ ተደራሽ፣ ተገማች፣ የረጋ እና ወደ ፊት የሚፈፀም መሆን እንደሚገባው ይገልፃሉ፡፡ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን መሰረት ያደረገው የህግ የበላይነት እይታ አንድ ህግ ቅቡል ለመሆን ከሥነ ስርዓታዊ መስፈርቶች በተጨማሪ የሞራል ቅቡልነት ያለው፣ ርትዕንና ሰብዓዊ መብቶችን እና ሌሎች ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ያከበረ መሆን ይገባዋል የሚል ነው፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀጽ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሌለው በመደንገግ በመንግስት ስልጣን ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው መንግስት ምንም እንኳ ህጋዊ መስፈርቶችን ያሟላ ህግ ቢያወጣም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ካላከበረ ህጉ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ መንግስት አላማውን ለማስፈፀም ወይም ለአገዛዝ እንዲመቸው መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያላከበረና መደበኛ የሕግ አወጣጥ ሥነ ስርዓትን የተከተለ ህግ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ስርዓት በህግ የተደገፈ ነበር፡፡ በሃገራችንም ፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ እና የምርጫ አዋጅ የገዥውን መንግስት ስልጣን ለማራዘም ሲባል የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድቡ በመሆናቸው መንግስት የህግ የባላይነትን በሚያስከብር መልኩ እያሻሻላቸው ይገኛል፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነት ሲባል በህግ አውጪው አካል መደበኛ የህግ አወጣጥ ስነ ስርዓትን ተከትሎ በወጣ ህግ መተዳደር ብቻ ሳይሆን ህጉ ባስገዳጅ ሁኔታ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ባከበረ መልኩ ስለመፅደቁ ትኩረት ይሻል ማለት ነው።

የህግ የባላይነት ፋይዳ እና አላባውያን

የሕግ የበላይነት የአስተዳደር መርህ ሲሆን ለሰላም ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም ውጤታማና ተአማኒነት ያለው የፍትህ አስተዳደር ተቋማት ለመገንባት በመሰረታዊነት የሚወሰድ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በዋነኛነት ግን ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ለማሳካት የተወጠነ ሃሳብ ነው፡፡

እነሱም፡-

የመንግስትን የዘፈቀደ የስልጣን አጠቃቀምን ለመገደብ፣

የዜጎችን የንብረት፣ የነፃነት እና የሕይወት መብት በሌሎች እንዳይጣስ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡

በአንድ ሀገር መንግስት ውስጥ የህግ የበላይነት ስለመኖሩ ማረጋገጭ የሚሆኑ መገለጫ አላባውያን የተለያየ ቢሆንም በአለም አቀፍ ደረጃ የህግ የበላይነትን የሚያከብሩ ሃገራትን ደረጃ(rule of law index) የሚያወጣው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጅክት(world justice project) የሚጠቀምባቸውን መለኪያዎች ከህገ መንግስታችን አኳያ የሚከተሉትን አምስት አላባውያን እናያለን፡፡

በህግ የተገደበ የመንግስት ስልጣ

ህጋዊነት

ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል

ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር

ሰላምና ደህነት

በሕግ የተገደበ የመንግስት ስልጣን

የመንግስት፣ የባለስልጣናቱና እንደራሴዎቹ ሥልጣን መገደብ ወይም መወሰን አለበት የሚለው የህግ የበላይነት መለኪያ መስፈርት ከሁለት ሺ ዓመት በፊት ጀምሮ ሲያቀነቅኑት የነበረ ሲሆን ዋና አላማውም መንግስት በዘፈቀደ ያለገደብ ልጓም እንደሌለው ፈረስ የሚፈነጭ ከሆነ የዜጎችን መብት በመጨፍለቅ ጨቋጭና አምባገነነ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ መንግስት መጠቀም ያለበት የስልጣን መጠን የሃገርን እና የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት እና መብት አክብሮ ለማስከበር በሚያስችል መልኩ መሆን ይገባዋል፡፡ መንግስት በህግ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በሚፈፅምበት ወቅት በህግ በተቀመጡ አሰራሮች አግባብ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ከተቃረነ በህግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም ህጉን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ፍላጎት ቢያድርባቸው ህግ የማውጣት ስልጣንን የሚገድቡ ወሰኖችን(constraints) በመጣስ ሊሆን አይገባም፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 9 ማንኛም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ህግ አውጪው የሚያወጣው ህግ ወይም ሕግ አስፈፃሚው የሚወስነው ውሳኔ ወይም ህግ ተርጓሚው አካል ህግ ሲተረጉም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር እንዳለበት በስልጣናቸው ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ይህን ገደብ የጣሰ ህግ፣ ውሳኔ እና የህግ ትርጉም ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የመንግስት አካላት በህግ በተሰጣቸው ስልጣን( separation of power) ብቻ እየሰሩ ስለመሆኑ ግልፅነትና ተያቂነት የሚያሰፍን የቁጥጥር ማድረጊያ መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 12 ማንኛውም ሃላፊና የህዝብ ተመራጭ ሃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ ቁጥጥርና ተጠያቂ ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል የሶስቱ የመንግሰት አካላት የእርስ በርስ ቁጥጥር መኖር( ለምሳሌ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55(17-18) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠሩበትን አግባብ ደንግጓል) ፣ ለሲቨል ማህበራትና ለሚዲያ ተጠያቂ በመሆን፣ የመንግስት ስልጣን በህግ አግባብ ብቻ እንዲተላለፍ በማድረግ(ህገ መንግስት አንቀጽ 9(3) ይመለከቷል) ወ.ዘተረፈ ይገኝበታል፡፡

ህጋዊነት

የህግ የባላይነት ማረጋገጫ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሕጋዊነት መርህ መኖር ሲሆን አንድ ህግ ከረቂቅ ጀምሮ ፀድቆ ተግባር ላይ በሚውልበት ወቅት ተደራሽ መሆኑ፣ ህጉ ግልፅና በቀላሉ የሚረዱት መሆኑ፣ ለውጥን የሚያስተናግድ፣ ተገማች የሆነ፣ ሊፈፀም የሚችል፣ በሁሉም ላይ በእኩል ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ እና ማስፈፀሚ ስርዓትና ተቋም ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡ አንድ የህግ ስርዓት እነዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ከሆነ መንግስት እና ዜጎች ለህጉ ይገዛሉ ተብሎ አይጠበቀም፡፡ ይህ መርህ መከበሩ ዜጎች ባልወጣ ህግ እንዳይቀጡና የወጡትንም ህጎች አክብረው የእለተ ተለት ህይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል፡፡ ህጉም ተገማች በመሆኑ ግብይት እንዲሳለጥ ይደርጋል፡፡ ምክንያቱም ትርፍና ኪሳራቸውን አስልተው እንዲገበያዩ ያስችላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የውል ህግ በመኖሩ ዜጎች ያለ ስጋት በነፃነት እንዲገበያዮ ዋስትና ይሰጣቸዋል፤ ዉሉን ያላከበረ ተገዶ እንዲፈፅም ወይም ካሳ እንዲከፍል ስለሚደርግ ለሌላኛው ወገን ዋስትና ይሆናል፡፡ የንብረት ህግ ዜጎች ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን አውጥተው ያፈሩትን ንብረት በነፃነት እንዲጠቀሙ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ የዚህ መርህ መስፈርቶች ህገ መንግስቱ ውስጥ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ ስለመንግስት አሰራር ግልፅነት እና ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆን በተመለከተ በሕገ መንግስቱን አንቀጽ 12(1) እና 25 እንደቅደም ተከተላቸው ተደንግገዋል፡፡

ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል

ነጻ የሆነ ፍ/ቤት የሕግ በላይነት መሰረታዊ ገፅታና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛው ባሕሪ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ነው፡፡ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በሕገ-መንግስት ወይም በሌላ ሕግ መደንገጋቸው ብቻ በራሱ ለመብቶች መረጋገጥ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ መብቶች እውን ይሆኑ ዘንድ ነፃ ፍ/ቤት መኖር አለበት፡፡ ነፃነት የሌለው ፍ/ቤት የሰዎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲረጋገጥ ሊያደርግ አይችልም፡፡

በዜጎችና በመንግስት እንዲሁም በሰዎች መካከል ባሉ ግንኙነቶች ሳቢያ የሚነሱ የፍትሐብሔር ወይም ወንጀል ክርክሮችን ገለልተኛና ነፃ ሆኖ እልባት ሊሰጥ የሚችል ፍ/ቤት በሌለበት የሕግ በላይነት ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ የሕግ በላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና መልካም አስተዳደር እውን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሰላምና ዘለቄታ ያለው ልማትም ዋስትና አይኖረውም፡፡ የዳኝነት ነፃነት ለኢንቨስትመንትና ለኢኮኖሚ እድገት መሰረት ነው፡፡ ባለሃብቱ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዲኖረው በአንድ ሀገር ውሰጥ የዳኝነት ነፃነት መስፈንና መረጋገት ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ስለዳኝነት ነፃነት አስፈላጊነት ላይ ምንም ክርክር የለውም፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 78 እና 79 ነፃ የዳኝነት አካል እንደተቋቋመ እና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት አካል፣ ከማንኛውም ባለስልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅእኖ ነፃ መሆናቸው እና ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት በህግ በመመራት እንደሚያከናውኑ ተደንግጓል፡፡ ጥያቄው ያለው የዳኝነት ነፃነት ስፋትና እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ ላይ ነው፡፡

ሠላም፣ ስርዓትና ደህንነት

የአንድ ሃገር መንግስት፣ ህዝብና ነዋሪዎች ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት መብትና ጥቅም መከበረ እና መረጋገጥ የህግ የባለይነት ዋነኛ ገፅታ ነው፡፡ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻቻለው በአገራዊ ደህንነት፣ በመንግስትና በህዝብ ጥቅም፣ በግለሰቦች ደህንነትና መብት ላይ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊት ዝግጅቶችንና ሴራዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ሲቻልና ወንጀሎቹ ከተፈፀሙ አጥፊዎችን በህግ ስርዓት ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብና ለማስቀጣት ሲቻል ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ፓለቲካ ድርጅቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራትና ማንኛውም ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በህገ መንግስቱና ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ የማከናውን የዳበረ ባህል ሲዳብሩ የምርጫ ውድድሮች ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካውና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ህግና ሥርዓትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ መንግስት ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ጉልበትን የመጠቀም(monopoly ofcoercive power) ብቸኛ መብት አለው፡፡ በመሆኑም ከህግ ከተፈቀደው ውጭ ዜጎች ወይም ሌሎች አካላት መብታቸውን ለማስከበር ሃይል የመጠቀም መብት የላቸውም፡፡ መንግሰት ሃገረ መንግስቱ የቆመበትን ሥርዓና ደህንነት ማስከበር አለበት ሲባል ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት የመከላከል ስራ መሰራት፣ ፓለቲካዊ ግጭቶችን(ሽብርተኝነት፣ አለመረጋጋትን፣ በታጠቁ ሃይሎች መካከል የሚደረግ ግጭትን) ውጤታማ በሆነ መልኩ መቀነስ እና የግል ችግርን ወይም በደልን ለመወጣት መደበኛውን የህግ ማስከበር ሥርዓት ከመከተል ይልቅ ሃይልን መጠቀም ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው አድርጎ አለመፈፀም(ለምሳሌ የደቦ ፍትህ) በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሰብዓዊ መብትና ነፃነቶች መከበር

ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የመነጩ የማጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡ ሃገራችን ህገ መንግስት የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩ ስለመሆኑ በመሰረታዊ መርህነት የተደነገገ ከመሆኑም በላይ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የፌደራል መንግስት የክልል ህግ አውጭ፣ አስፈፃሚና የዳኝነት አካል በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት በተካተቱ የሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ ነፃነቶች ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ስለመሆኑ በአንቀጽ 13(1) ተደንግጓል፡፡ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የሚወጣው አስፈላጊውን የህግ፣ የአስተዳደርና ሌሎች እርምጃዎች በመዉሰድ ነው፡፡ መንግስት ከዜጎቹ ጋር ባለው የቀጥታ ግንኙነት እንዲሁም ዜጎች ባላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም የመንግስት ባለስልጣናትና ሰራተኞች ስልጣንና ሃላፊነታቸውን አላግባብና ከህግ ውጭ በመጠቀም የሚፈፀሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊቶችን እንዲሁም ሰዎች ባላቸው የጎንዮሽ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብትና ነፃነት የሚጥሱ ድርጊቶች የወንጀል ተጠያቂነትና ሃላፊነት የሚያስከትሉ ድርጊቶች መሆናቸውን በመደንገግ፣ በመከላከል እና ጥሰቱ ተፈፅሞ ሲገኝ በተሟላ ሁኔታ በወንጀል ፍትህ ስርዓቱ እንዲፈፀም በማድረግ መንግስት ሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታውን በመወጣት የህግ የባለይነትን ማረጋገጥ አለበት፡፡

የሕግ የባለይነትን ለማረጋገጥ ምን ይደረግ ?

በአንድ ሃገር ውስጥ የህግ የበላይነት መኖር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ካልሆነ በስተቀረ ከላይ የተመለከቱት የህግ የበላይነት መገለጫዎች ሙሉ በሙሉ የተከበረበት ሃገር የለም፡፡ የህግ የበላይነት በጊዜ ሂደት የሚገነባ እና የጋራ ባሕል መገለጫ ይሆናል፡፡ መንግስት እና ዜጎች ሕጎች የእሴቶቻቸው መገለጫ እና ጥቅማቸውን ለማስከበር የወጡ መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ህጎች በማክበርም ሆነ በማስከበር የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል፡፡

Contact us via hihoney3@gmail.com

ማሰቃየትን ስለሚከለክሉ የኢትዮጵያ ህጎች

                                                        torture-report
በጢሞቲዎስ ዋርጎ
ክልል ዓቃቤ ህግ
የማሰቃየት ትርጉም
የተባበሩት መንግስታት በ1948 ማሰቃየትና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸዉ ሰብአዊነት የጎደላቸዉ አዋራጅ ሆኑ አያያዞችንና ቅጣቶችን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት በአጭሩ «ማሰቃትን የሚከለክል ስምምነት» ተብሎ የሚጠራዉን የቃል ኪዳን ሰነድ አፅድቆ ስምምነቱም በበርካታ ሀገሮች ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ኢትዮጵያም በ1986 ዓ.ም የዚህ ስምምነት አባል ሀገር ሆናለች፡፡ ይህ ስምምነት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 9/4/ መሰረት የኢትዮጵያ ህጎች አካል ነዉ፡፡
ዓለም ዓቀፍ ማሰቃየትን የሚከለክለው የቃል ኪዳን ስምምነት በአንቀጽ 1 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ ማሰቃት ምን እንደሆነ በመግለጽ ይጀምራል፡፡ ይኸዉም ከራሱ ወይም ከሶስተኛ ወገን መረጃ ለማግኘት ወይም እንዲናዘዝ /እንዲለፈልፍ/ ለማድረግ በአንድ ሰዉ ላይ ሆን ብሎ የአካል ወይም የአእምሮ ስቃይ የሚያደርስ ድርጊት መፈጸም፤ እራሱ ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን ለፈጸመዉ ወይም ፈጽሟል ተብሎ በተጠረጠረበት ድርጊት ለማስፈራራት ወይም ለማስገደድ ወይም በማናቸዉም በልዩነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ የመንግስት ስልጣን ይዞ የሚሰራ ሰዉ ወይም በእርሱ ተነሳሽነት፣ስምምነት ወይም አዉቆ እንዳላወቀ በመምሰል በማሰቃት የሚፈጸም ማንኛዉም የማሰቃት ድርጊት ማሰቃየት ይባላል በማለት ይተረጉመዋል፡፡
ከዚህ ትርጉም አራት አበይት ጉዳዮች ተመልክተዋል፡፡ እነዚህንም እንደሚከተለው በዝርዝር እናያለን፡፡
የመጀመሪያዉ የድርጊቱን ዓላማ ይመለከታል፤ ይሀዉም ማሰቃት/ቶርቸር/ተብሎ የሚወሰደዉ ለስቃይ መነሻ የሆነዉ ድርጊት ወይም ስቃዩ እንዲደርስ የተደረገበት ዓላማ ስቃይ ከሚደርስበት ወይም ከተፈፀመበት ሰዉ ከራሱ ወይም ከሌላ ሶስተኛ ወገን መረጃ ለማግኘት ወይም ይህ ሰዉ እንዲናዘዝ ተብሎ ሲፈፀም ነዉ፡፡ ይህ ማለት በሰዉ ላይ ስቃይ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ሁሉ ማሰቃየት/ቶርቸር/ አይሆኑም፡፡ ስቃይ የፈጠሩት ድርጊቶች ከተሰቃዩ ወይም ከሌላ ሶስተኛ ሰዉ አስገድዶ መረጃ ለማግኘት ተብሎ የሚደረጉ መሆን አለባቸዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ መርማሪ ፖሊስ አንድን ተመርማሪ የተጠረጠረበት ድርጊት በተመለከተ ሲመረምር እዉነቱን አዉጣ በማለት ከደበደበዉ ማሰቃት ተፈጸመ ማለት ነዉ፡፡
ሁለተኛዉ ስቃዩን የሚያደርሱ ድርጊቶች በተሰቃዩ ላይ የሚያደርሱትን የስቃይ ዓይነት ይመለከታል፤ ስቃይ የሚያደርሱ ድርጊቶችና ማሰቃት የሚባሉት የሚያደርሱት የስቃይ ዓይነት አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ሊሆን ይችላል፡፡ አካላዊ ስቃይ የሚባለዉ በተሰቃዩ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የአካል ጉዳት ሲደርስበት ነዉ፡፡ አእምሮአዊ የሚባለዉ ተሰቃዩ ቀጥተኛ የሆነ የአካል ጉዳት ባይደርስበትም በተፈጸሙበት ደርጊቶች ምክንያት የአእምሮ ወይም የስነልቦና ጉዳት ሲደርስበት ነዉ፡፡ ለምሳሌ፤ ፖሊስ አንድን ተመርማሪ የተጠረጠረበት ድርጊት ሲመረምር እዉነቱን እስከሚያወጣ ድረስ በማለት የተመርማሪዉን ቤተሰብ ቢያስርበት ይህ ሁኔታ በተመርማሪዉ ላይ ስነልቦናዊ ጉዳት ያደርሳል፡፡
ሶስተኛዉ በተሰቃዩ ላይ የሚፈጸሙት ድርጊቶች የሚከናወንበት መንገድ ይመለከታል፤ ይኸዉም አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ስቃይ በማስፈራራት፣በማስገደድ ወይም ሌላ ዓይነት ድርጊት በማድረስ ሊፈፀም ይችላል፡፡ ስቃይ ፈፃሚዉ ራሱ በቀጥታ ድርጊቱን ባይፈጸምም ሌሎች ሲፈጸሙ አይቶ እንዳላየ ቢመስል ድርጊቱን እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡ለምሳሌ፤ መርማሪ ፖሊስ ተመርማሪዉን ቢደበድበዉ፣ሲደበድበዉ እንደሚያድር ቢገልጽለት፣ እዉነቱን ካልተናገረ ከባድ የሆነ የእስር ቅጣት እንደሚደርስበት ወይም ከልጆቹ አንዱ ላይ የአካል ጉዳት እንደሚደርስባቸዉ ቢገልጽለት ወዘተ በእነዚህ መንገዶች ማሰቃት ተፈፅሟል ማለት ነዉ፡፡
አራተኛዉ ከፈጻሚዉ አኳያ ይታያል፤ የማሰቃት ድርጊት ተፈጸመ የሚባለዉ ማሰቃትን የፈጸሙት በዋናነት የመንግስትን ስልጣን የያዙ አካላት ሲሆኑ ነዉ፡፡ለምሳሌ የድርጊቱ ፈጻሚ መርማሪ ፖሊስ ሲሆን ፖሊስ ደግሞ የመንግስት አካል በመሆኑ የተፈጸመዉ ድርጊት የማሰቃየት ተግባር ነዉ ማለት ነዉ፡፡
ማሰቃየትን የሚከለክሉ የኢትዮጵያ ህጎች
ሀ) ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 9(4) እና አንቀጽ 13(2) ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎች የሀገሪቱ ህጎች አካል መሆናቸውን ይደነግጋሉ፡፡ እነዚህ አንቀጾች ማሰቃየትን የሚከለክለው ስምምነት የሀገር ውስጥ ህግ ሆኖ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህገመንግስቱ ራሱ ማሰቃየትን ይከለክላል፡፡
ማሰቃየትን የሚመለከተው የህግ መንግስቱ ክፍል አንቀጽ 18 ሲሆን ይህ አንቀጽ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርዱ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡
ህገ መንግስቱ ማሰቃየትን/ቶርቸርን/በግልጽ አይጠቅስም፡፡ ነገር ግን አንቀጽ 18 ላይ የተከለከሉት ድርጊቶች ስንመለከት ባጠቃላይ ማንኛውም ጭካኔ የተሞላባቸውና ኢሠብአዊ ድርጊቶችን የሚከለክል በመሆኑ ማሰቃየትን/ ቶርቸርን/ የመሰለ ኢ-ሰብአዊና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የሚከለክል ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ለ) የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ
በ1954 ዓ/ም የወጣው የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ አንቀጽ 31 ፖሊስ በምርመራ ወቅት በተመርማሪው ላይ ማድረግ የሌለበትን ድርጊቶች ይዘረዝራል፡፡ የማሰቃየትን ትርጉም ቀደም ብለን ስንመለከት ማሰቃየት ከሚፈጸምባቸው ሁኔታዎች አንዱ ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው ስቃዩ ከሚደርስበት ሰው ላይ መረጃ ለማግኘት ሲል የሚያደርገው እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ ከነዚህም ሁኔታዎች አንዱ ፖሊስ ተጠርጣሪን በሚመረምርበት ወይም በሚጠይቅበት ወቅት ነው፡፡ የፖሊስ የምርመራ ተግባር በህግ ካልተገዛና ገደብ ካልተደረገበት ተመርማሪውን ግለሰብ ለስቃይ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ይህንንም ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 31(1) ፖሊስ የተመርማሪውን ቃል ሲቀበል ተመርማሪውን መደለል ወይም እንዲደልል ማድረግ፣ የማስፈራራት ወይም የሀይል ስራ ወይም ሌሎች ከሕግ ውጪ ያለ ዘዴዎች መፈጸም ወይም ማድረግ አይችልም በማለት የሚደነግገው፡፡ምንም እንኳን ድንጋጌው ማሰቃየት ወይም ቶርቸርን በግልጽ ባይጠቅስም ማሰቃየት አሰቃቂ የሆነ የሀይል ድርጊት በመሆኑ ፖሊስ ምርመራ በሚያካሄድበት ወቅት ይህንን ድርጊት መፈጸም እንደሌለበት ህጉ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ማሰቃየት ወይም በአንቀጽ 31(1) የተዘረዘሩትን ማናቸውንም ድርጊት በመፈጸም የተገኘ ማስረጃ በህግ ፊት ተቀባይነት የለውም
ሐ/ የወንጀል ሕግ
በ1996 ዓ/ም ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 424 የማስፈራራት ወይም ከሰብአዊ ርህራሄ ውጪ ወይም ለሰው ልጅ ክብር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት የፈጸመ በተለይም ድብደባ፣የመንፈስ ስቃይ፣የጭካኔ ተግባር ያደረሰ የመንግስት ሰራተኛ በእስራት ወይም በመቀጫ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ አንቀጹ ሰፋ ያለ ሁኔታዎችን የሚያካትት ሲሆን በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ማሰቃየት/ቶርቸር/ የሚካተት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ይህ አንቀጽ የወንጀል አድራጊውን ብቻ ሳይሆን ለወንጀል መፈጸም ተጠያቂ የሆነውን ትእዛዝ የሰጠውን ባለስልጣን ጭምር የሚቀጣ ነው፡፡ በትእዛዝ ሰጪው ባለስልጣን ላይ የተጣለው ቅጣት ከፈጻሚው ቅጣት ከበድ ያለ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቶርቸር የፈጸመ ማንኛውም ባለስልጣን ከተጠያቂነት የማያመልጥ መሆኑንም ህጉ በሚገባ ያስገነዝባል፡፡
ማሰቃየትን የሚከለክሉ ህጎችን ከማስፈጸም አኳያ የዓቃቤ ህግ ሚና
ሀ) ህጎችን የማስተማር ግዴታ
ማሰቃየትን ለማስወገድ በቶርቸር ስምምነት በአንቀፅ 10 ከተመለከቱት እርምጃዎች መካከል ማሠቃየትን በተመለከተ ትምህርት እና ስልጠና መስጠት አንዱ ነው፡፡ ማሠቃየትን በዋናነት ማስቀረት የሚቻለው ድርጊቱ እንዳይፈፀም በመከላከል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ማሠቃየትን ሊፈፀሙ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ሰዎችን ለይቶ ማሠቃየት አስከፊ፣ አሰቃቂና ኢ-ሠብአዊ ድርጊት መሆኑን እና ይህም ማስተማር የተከለከለና የተኮነነ ድርጊት መሆኑን በግልፅና በቅድሚያ ማሳወቅ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ባለማወቅ ማሠቃየትን ሊፈፅሙ የሚችሉ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ከዚህም አልፎ ማሠቃየትን በተመለከተ በቂ እውቀት እንዲሰራጭና ድርጊቱን በአንድነት ለመኮነንና ለመከላከል ይቻላል፡፡ ስለዚህ ዓቃቢያነ ህግ ስቃይን የሚከለክለው ስምምነት ይዘት በየደረጃዉ ላሉት የህብረተሰብ አካላት በአጠቃላይ እንዲሁም በስራ አጋጣሚ የማሰቃየት ተግባር ለመፈጸም ተጋላጫ ለሆኑ የመንግስት አካላትን በተላይ በተለያየ ዘዴዎች ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት የድርጊቱን የመከላከል ሀላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡
ለ) የወንጀል ምርመራ የመምራት እና ህጋዊነቱን የማረጋገጥ ግዴታ

በወንጀል ተጠርጥረዉ ተይዘው ወይም ታስረው የሚገኙ ግለሰቦች የሚደረግላቸው አያያዝ፣ የምርመራ ዘዴዎችን ወዘተ… ማሰቃየትን ከማስወገድ አኳያ በየጊዜው የዓቃቤ ህግን ጥብቅ ክትትል የሚፈለግ ነዉ፡፡ በ2003 ዓ.ም የወጣዉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ የወንጀል ምርመራ የመምራት ሀላፊነት የዓቃቤ ህግ እንደሆነ ሀገራዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡በመሆኑም ዓቃቢያነ ህግ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገዉን የወንጀል ምርመራ በመምራት ብሎም በተመርማሪዉ ላይ የሚደረገዉን ምርመራ ዓለም አቀፍ የቶርቸር ስምምነት መለኪያዎችን የሚያሟሉ ህጋዊ ሂደቶችን የተከተለ ስለመሆኑ የማረጋገጥ ሀላፊነት አለባቸዉ፡፡
ሐ/ የግለሰብን አቤቱታ የማስተናገድ እና ምርመራ የማከናወን ግዴታ

ማንኛውም ግለሰብ ማሠቃየት ተፈፅሞብኛል ብሎ አቤቱታ ሲያቀርብ ዓቃቢያነ ህግ አቤቱታ ተቀብሎ ራሱ ወይም ከመርማር ፖሊስ ጋር በመሆን በአፋጣኝ የመመርመር ግዴታ አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አቤቱታ ያቀረበው ግለሰብ እና ምስክሮቹ የማጉላላትና የማስፈራራት ድርጊቶች እንዳይፈፀምባቸው ተገቢዉ የህግ ጥበቃ ሊደረግላቸዉ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ዓቃቢያነ ህግ በሚሰሯቸዉ አከባቢ/በግዛት ክልላቸው/ ውስጥ በወንጀል ተጠርጥረዉ ምርመራ በሚደረግባቸዉ ተጠርጣሪዎች ማሰቃት/ቶርቸር/ተፈፅሟል ብለው ሲጠረጥር ወይም ሲያምን አስፈላጊው የማጣራትና የመመርመር እርምጃ እንዲደረግ የማድረግ ሀላፊነት እና ግዴታ አለባቸዉ፡፡ ይህ እርምጃ አፋጣኝና ከአድልዎ ነፃ መሆን አለበት፡፡

“የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው”: ዳራና አንዳንድ ነጥቦች

ሃዋ ሙሐመድ፣ እናቴዋ!
(ከጉዞ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
ከደሴ ወደ ራያ ቆቦ በሚኒባስ ተሳፍሬ እየተጓዝኩ ነው። ወደ ትውልድ ቀየየ ከረዥም ጊዜ በኋላ ለሃዘን ስለነበር የምሄደው በመስኮቱ ወደ ውጭ እየተመለከትኩ በውስጤ ብዙ ነገር እያሰላሰልኩ (ባርባር እያለኝ) ከአጠገቤ የተቀመጡ ጉፍታ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉ ደርባባ ሁለት ሙስሊም እናቶች የሚያወሩትን ልብ ብየ አልሰማቸውም ነበር። አንዷ እናት ለምታወራው ነገር ማዋዣ ይሆን ዘንድ “የምን ነገር ማንዛዛት ነው፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ሲባል ሰምተሽ አታውቂም” ስትል ድንገት ሰማኋት። የህግ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ የማስረጃ ህግ ትምህርት ውስጥ በወንጀል ጉዳይ የአንድን ማስረጃ በተለይም የእምነት ቃል ቅቡልነት(admissibility) የሚወስነው ሂደቱ(the means justifies the end) ወይስ ውጤቱ (the end justifies the means)የሚል የጦፈ ክርክር እናደርግ ነበር። የኋላኛውን ሃሳብ የምናቀነቅን ተማሪዎች የአንድ የማስረጃ ውጤት ፍትህ ላይ የሚያደርስ ከሆነ እንዴት ተገኘ የሚለው ሥነ ስርዓታዊ ሂደቱ አያሳስብም። ሂደቱ ችግር አለበት ብለህ ማስረጃውን ውድቅ ከምታደርግ ይልቅ በሂደቱ ላይ ህገወጥ ድርጊቱን የፈፀመውን መርማሪ በወንጀልና በፍትሃብሄር ተጠያቂ በማድረግ ወደፊት ተመሳስይ ድርጊት እንዳይፈፀም መቀጣጫ ማድረግ ይገባል እንላለን። ለዚህ መከራከሪያ ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው እያልን ክርክራችንን በምሳሌያዊ አባባል እናጅባለን። አሁንም ቀጥሏል፣ ግን አቋሜን ቀይሪያለሁ። ሆኖም ግን ስለዚህ ምሳሌያዊ አባባል አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ ሰምቼ አላውቅም ነበር። ታዲያ እኔም ከቁዘማየ ነቅቼ በወጋቸው መሃል ጣልቃ ስለገባሁ ይቅርታ ጠይቄ (የኛ ሰው ወግ አደናቃፊን “ምን እንደ እርጎ ዝምብ ጥልቅ ትላለህ ብሎ ይገስፃል፣ እስኪ ልጨርስ አድምጥ ሲልህ ነው) ጥያቄን አቀረብኩ “ይህ አባባል ለምን ተባለ፣ መነሻው ምንድነው ብየ ጠየኩ?”። ዝምታ ሆነ። ተያየን። አንዷ እናት ዝምታውን እንድህ ስትል ሰበረችው። ድሮ ነው አሉ። አንዲት የባርያ አሳዳሪ ባርያዋን ሁለት ቁና ጤፍ እንድትፈጭላት ጤፉን ከጎተራው ስፍራ ሰጥታት ወደ ጓዳ ተመለሰች። ባርያዋም በስራ ጫና በጣም ደክሟት ስለነበር የወፍጮውን መጅ መግፋት ተስኗት “እመቤቴ ማርያም አንቺው ያረግሽ አርጊው” ብላ እተማጠነች እያለ እንቅልፍ ሸለብ አረጋት። ከእንቅልፏ ስትነቃ ቁናው በዱቄት ተሞልቶ አገኘችውጭ። ደነገጠች፣ ጦለቴ ደርሶ ነው ብላ አመነች። ዱቄቱን ለአሳዳሪዋ አስረከበች ሆኖም ግን አሳዳሪዋ በዚህ ፍጥነት እንዴት ይሄን ልትፈጭ ቻልሽ? እንደውም የወፍጮውን ድምፅ አልሰማሁም? ይሄን ዱቄት አልቀበልም ጤፌን መልሽ አለቻት። ባርያዋም ግራ ገባት እንዳትመልስ ምንም የላት፣ ቢጨንቃት ዳኛ ይፍረደን አለች። ይፍረንደን፣ አለች መልሳ አሳዳሪዋ። ተያይዘው ወደ አጥቢያ ዳኛ ሆዱ። ጉዳዩን አስረዱ። የአጥቢያ ዳኛው የአሳዳሪዋን የክርክር ሃሳብ በመደገፍ የሾይጣን ስራ ካልሆነ በስተቀረ ወፍጮ ሲፈጭ ድምፅ ሳያወጣ እህል አይፈጭም ስለዚህ ሁለት ቁና ጤፉን መልሽ ብሎ ፈረደ። መቼስ የፍርድ ባለእዳ መሆን አስጨናቂ ነውና አውጥታ አውርዳ “እረኛ ይፍረድን” ብላ ተማፀነች። ምን ገዶኝ አለች አሳዳሪዋ። ለእረኛው ዝርዝሩ ተነገረው የራሱን ፍርድ እንዲህ ሲል ገለፀው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው”። “ዋናው ሁለት ቁናው ጤፍ ሳይጎል መፈጨቱ እንጂ በማን፣ እንዴት እና የት ተፈጨ የሚለው አያሳስብም ብሎ ድሃዋን ከጭንቀት ታደጋት ” ይባላል፣ ገምሻራየዋ ታሪኩ ይኽው ነው። በቅንነት የተሞላው የትረካቸው ለዛ ሃዘኔን አስረሳኝ። ሙስሊም ሆነው ሳለ የዘመኑ የእኛና እነሱ ትርክት ሰለባ ሳይሆኑ በቅንነት የእመቤቴ ማርያምን ስም እየጠቀሱ ተአምረ ማርያምን (እንደማንበብ ያህል) ተረኩልኝ። ይህ አልገረመኝም ምክንያቱም ወሎ እንዲህ ነው። የሚጠቅመውን የራሱ ያደርገዋል። የገሌነው ብሎ ጎራ አይለይም፤ አያከርም። ክርስቲያኑም እንደዛው። ብዙ ክርስቲያኖች ጀማ ንጉስ ለመውሊድ ሄደው ዱኣ እስደርገው ሲመለሱ አይቻለሁ፣ እኔም ኑሬበታለሁ። ይህ ለዘመናት የዳበረ የሕይዎት ዘይቤ ነው እንዲህ በዋዛ የማይፈታ።
ወጋችንን ቀጠልን። ትንሽ አሰብኩና፣ ይህን አባባል አላምንበትም። ድሃዋን እናት ከጭንቅ ቢገላግላትም በውስጡ ብዙ ችግር አለበት። በዚህ ዘመን ልንጠቀምበት አይገባም አልኳቸው። “መቼም የዘመኑ ልጆች ጉዳችሁ አያልቅም” ብለው ትክ ብለው ተመለከቱኝ፣ እስኪ ተናገር እንስማህ መሆኑ ነው። ስንፍናን፣ ሌብነትንና ህገወጥ አሰራርን ወ.ዘ.ተረፈ እንዲንሰራፋ ያበረታታል። በዚህም እንደጉዳዩ ሁኔታ ግለሰቦች፣ ሃገር፣ መንግስትና ህዝብ ይጎዳል። ወደፊት እንዳይራመዱ ገድቦ ይይዛል። አለፍ ሲልም ሃገር ያፈርሳል፣ ጠባቂ መከታ መንግስት እንዳይኖር ያደርጋል። ሰው ያለውን ጉልበት፣ እውቀት፣ ጊዜውንና ገንዘቡን አቀናጅቶ እንዳይሰራ ያደርገዋል፤ በአቋራጭ መበልፀግን ይመኛል። ትላንት እዚህ ግባ የማይባል ገቢ የነበረው ድንገት የናጠጠ ቱጃር ሲሆን ከየት፣ እንዴት እና መቼ ይህን ንብረት አፈራው ተብሎ ላይጠየቅ ነው? የወንጀል ፍሬ ቢሆንስ? በሌላ በኩል ለፍቶ ደክሞ በላቡ ሳያመርት፣ ሳይሰራ የሌሎችን እንዲያማትር ያደርጋል። ያሰንፋል፣ ክፉ በሽታ ነው። የመንግስት አካላትም በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት መወጣት ያለባቸው በህግ የተደነገጉ የአሰራር ሥርዓቶችን አክብረው መሆን ይገባቸዋል። የግብር ይውጣ አሰራር በጊዜ ሂደት ተጠያቂነት ያስቀራል፣ ስርዓት ያፈርሳል። ለአብነት ያህል ፓሊስ የወንጀል ተጠርጣሪ ሲያስር ወይም ቃል ሲቀበል በሥነ ስርዓት ህጉ የተቀመጡ የተከሳሽ መብቶችን ባከበረ መልኩ መሆን ይገባዋል። ተጠርጣሪውን መደብደብ፣ ማሰቃየትና ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ነገር መፈፀም የለበትም። ከድብደባው ስቃይ ለማምለጥ ሲል ያልፈፀመውን ወንጀል ፈፅሜያለው ቢልስ? ንፁህ ሰው ወንጀለኛ አድርገን ትክክለኛ ወንጀል ፈፃሚዎችን ነፃ ልናደርግ አይደለም ወይ? በድብደባው ምክንያት ሕይወቱን ቢያጣ ወይም በአካሉ ላይ ቋሚና ግዚያዊ ጉዳት ቢደርስበትስ? ለዚህ ችግር ማን ነው ተጠያቂው? ዜጎች በፍትህ ተቋሞቻችን ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይህ ሁሉ ተጠረቃቅሞ ሃገር በህግ የበላይነት ሳይሆን በሰዎች የበላይነት እንድትመራ ያደርጋል። የወገን አለኝታ የሆኑ ተቋሞች እንዳይኖሩን ያደርጋል። መዘዙ ብዙ ነው። እናቶቼ ስሙኝማ…የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው አይበጀንም ይቅርብን አልኳቸው። አንደኛዋ እናት፣ “እኛ ይህን ሁሉ ጉድ መች አወቅንና እንደው ዝም ብለን አፋችን ያመጣልንን እናወራለን እንጁ…” እያሉ ..መኪናው ቆመ.. ረዳቱ… መርሳ ወራጅ ሲል.. ሁለቱ እናቶች ለመውረድ እቃቸውን እየሰበሰቡ….”ገምሻራየዋ” በል በደህና ግባ፣ መንገዱ ቀና ይሁንልህ፣ ቤተሰቦችህን በኸይር አግኛቸው ብለው መርቀው..ተሰናብተውኝ ወረዱ። መኪናው ሳይንቀሳቀስ በፊት ድምፄን ከፍ አድርጌ..ማዘር… ስመዎን አልነገሩኝም እኔ ኃይለማርያም እባላለሁ የአንቱስ?…መከናው ተንቀሳቀሰ..”ሃዋ መሃመድ” የሚል ድምፅ ጆሮየ ላይ ደረሰ።
ሃዋ ኑልኝ፣ እድሜዎ ይርዘም አቦ። አሜን።

“የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው”: ዳራና አንዳንድ ነጥቦች

ሃዋ ሙሐመድ፣ እናቴዋ!
(ከጉዞ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
ከደሴ ወደ ራያ ቆቦ በሚኒባስ ተሳፍሬ እየተጓዝኩ ነው። ወደ ትውልድ ቀየየ ከረዥም ጊዜ በኋላ ለሃዘን ስለነበር የምሄደው በመስኮቱ ወደ ውጭ እየተመለከትኩ በውስጤ ብዙ ነገር እያሰላሰልኩ (ባርባር እያለኝ) ከአጠገቤ የተቀመጡ ጉፍታ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉ ደርባባ ሁለት ሙስሊም እናቶች የሚያወሩትን ልብ ብየ አልሰማቸውም ነበር። አንዷ እናት ለምታወራው ነገር ማዋዣ ይሆን ዘንድ “የምን ነገር ማንዛዛት ነው፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ሲባል ሰምተሽ አታውቂም” ስትል ድንገት ሰማኋት። የህግ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ የማስረጃ ህግ ትምህርት ውስጥ በወንጀል ጉዳይ የአንድን ማስረጃ በተለይም የእምነት ቃል ቅቡልነት(admissibility) የሚወስነው ሂደቱ(the means justifies the end) ወይስ ውጤቱ (the end justifies the means)የሚል የጦፈ ክርክር እናደርግ ነበር። የኋላኛውን ሃሳብ የምናቀነቅን ተማሪዎች የአንድ የማስረጃ ውጤት ፍትህ ላይ የሚያደርስ ከሆነ እንዴት ተገኘ የሚለው ሥነ ስርዓታዊ ሂደቱ አያሳስብም። ሂደቱ ችግር አለበት ብለህ ማስረጃውን ውድቅ ከምታደርግ ይልቅ በሂደቱ ላይ ህገወጥ ድርጊቱን የፈፀመውን መርማሪ በወንጀልና በፍትሃብሄር ተጠያቂ በማድረግ ወደፊት ተመሳስይ ድርጊት እንዳይፈፀም መቀጣጫ ማድረግ ይገባል እንላለን። ለዚህ መከራከሪያ ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው እያልን ክርክራችንን በምሳሌያዊ አባባል እናጅባለን። አሁንም ቀጥሏል፣ ግን አቋሜን ቀይሪያለሁ። ሆኖም ግን ስለዚህ ምሳሌያዊ አባባል አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ ሰምቼ አላውቅም ነበር። ታዲያ እኔም ከቁዘማየ ነቅቼ በወጋቸው መሃል ጣልቃ ስለገባሁ ይቅርታ ጠይቄ (የኛ ሰው ወግ አደናቃፊን “ምን እንደ እርጎ ዝምብ ጥልቅ ትላለህ ብሎ ይገስፃል፣ እስኪ ልጨርስ አድምጥ ሲልህ ነው) ጥያቄን አቀረብኩ “ይህ አባባል ለምን ተባለ፣ መነሻው ምንድነው ብየ ጠየኩ?”። ዝምታ ሆነ። ተያየን። አንዷ እናት ዝምታውን እንድህ ስትል ሰበረችው። ድሮ ነው አሉ። አንዲት የባርያ አሳዳሪ ባርያዋን ሁለት ቁና ጤፍ እንድትፈጭላት ጤፉን ከጎተራው ስፍራ ሰጥታት ወደ ጓዳ ተመለሰች። ባርያዋም በስራ ጫና በጣም ደክሟት ስለነበር የወፍጮውን መጅ መግፋት ተስኗት “እመቤቴ ማርያም አንቺው ያረግሽ አርጊው” ብላ እተማጠነች እያለ እንቅልፍ ሸለብ አረጋት። ከእንቅልፏ ስትነቃ ቁናው በዱቄት ተሞልቶ አገኘችውጭ። ደነገጠች፣ ጦለቴ ደርሶ ነው ብላ አመነች። ዱቄቱን ለአሳዳሪዋ አስረከበች ሆኖም ግን አሳዳሪዋ በዚህ ፍጥነት እንዴት ይሄን ልትፈጭ ቻልሽ? እንደውም የወፍጮውን ድምፅ አልሰማሁም? ይሄን ዱቄት አልቀበልም ጤፌን መልሽ አለቻት። ባርያዋም ግራ ገባት እንዳትመልስ ምንም የላት፣ ቢጨንቃት ዳኛ ይፍረደን አለች። ይፍረንደን፣ አለች መልሳ አሳዳሪዋ። ተያይዘው ወደ አጥቢያ ዳኛ ሆዱ። ጉዳዩን አስረዱ። የአጥቢያ ዳኛው የአሳዳሪዋን የክርክር ሃሳብ በመደገፍ የሾይጣን ስራ ካልሆነ በስተቀረ ወፍጮ ሲፈጭ ድምፅ ሳያወጣ እህል አይፈጭም ስለዚህ ሁለት ቁና ጤፉን መልሽ ብሎ ፈረደ። መቼስ የፍርድ ባለእዳ መሆን አስጨናቂ ነውና አውጥታ አውርዳ “እረኛ ይፍረድን” ብላ ተማፀነች። ምን ገዶኝ አለች አሳዳሪዋ። ለእረኛው ዝርዝሩ ተነገረው የራሱን ፍርድ እንዲህ ሲል ገለፀው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው”። “ዋናው ሁለት ቁናው ጤፍ ሳይጎል መፈጨቱ እንጂ በማን፣ እንዴት እና የት ተፈጨ የሚለው አያሳስብም ብሎ ድሃዋን ከጭንቀት ታደጋት ” ይባላል፣ ገምሻራየዋ ታሪኩ ይኽው ነው። በቅንነት የተሞላው የትረካቸው ለዛ ሃዘኔን አስረሳኝ። ሙስሊም ሆነው ሳለ የዘመኑ የእኛና እነሱ ትርክት ሰለባ ሳይሆኑ በቅንነት የእመቤቴ ማርያምን ስም እየጠቀሱ ተአምረ ማርያምን (እንደማንበብ ያህል) ተረኩልኝ። ይህ አልገረመኝም ምክንያቱም ወሎ እንዲህ ነው። የሚጠቅመውን የራሱ ያደርገዋል። የገሌነው ብሎ ጎራ አይለይም፤ አያከርም። ክርስቲያኑም እንደዛው። ብዙ ክርስቲያኖች ጀማ ንጉስ ለመውሊድ ሄደው ዱኣ እስደርገው ሲመለሱ አይቻለሁ፣ እኔም ኑሬበታለሁ። ይህ ለዘመናት የዳበረ የሕይዎት ዘይቤ ነው እንዲህ በዋዛ የማይፈታ።
ወጋችንን ቀጠልን። ትንሽ አሰብኩና፣ ይህን አባባል አላምንበትም። ድሃዋን እናት ከጭንቅ ቢገላግላትም በውስጡ ብዙ ችግር አለበት። በዚህ ዘመን ልንጠቀምበት አይገባም አልኳቸው። “መቼም የዘመኑ ልጆች ጉዳችሁ አያልቅም” ብለው ትክ ብለው ተመለከቱኝ፣ እስኪ ተናገር እንስማህ መሆኑ ነው። ስንፍናን፣ ሌብነትንና ህገወጥ አሰራርን ወ.ዘ.ተረፈ እንዲንሰራፋ ያበረታታል። በዚህም እንደጉዳዩ ሁኔታ ግለሰቦች፣ ሃገር፣ መንግስትና ህዝብ ይጎዳል። ወደፊት እንዳይራመዱ ገድቦ ይይዛል። አለፍ ሲልም ሃገር ያፈርሳል፣ ጠባቂ መከታ መንግስት እንዳይኖር ያደርጋል። ሰው ያለውን ጉልበት፣ እውቀት፣ ጊዜውንና ገንዘቡን አቀናጅቶ እንዳይሰራ ያደርገዋል፤ በአቋራጭ መበልፀግን ይመኛል። ትላንት እዚህ ግባ የማይባል ገቢ የነበረው ድንገት የናጠጠ ቱጃር ሲሆን ከየት፣ እንዴት እና መቼ ይህን ንብረት አፈራው ተብሎ ላይጠየቅ ነው? የወንጀል ፍሬ ቢሆንስ? በሌላ በኩል ለፍቶ ደክሞ በላቡ ሳያመርት፣ ሳይሰራ የሌሎችን እንዲያማትር ያደርጋል። ያሰንፋል፣ ክፉ በሽታ ነው። የመንግስት አካላትም በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት መወጣት ያለባቸው በህግ የተደነገጉ የአሰራር ሥርዓቶችን አክብረው መሆን ይገባቸዋል። የግብር ይውጣ አሰራር በጊዜ ሂደት ተጠያቂነት ያስቀራል፣ ስርዓት ያፈርሳል። ለአብነት ያህል ፓሊስ የወንጀል ተጠርጣሪ ሲያስር ወይም ቃል ሲቀበል በሥነ ስርዓት ህጉ የተቀመጡ የተከሳሽ መብቶችን ባከበረ መልኩ መሆን ይገባዋል። ተጠርጣሪውን መደብደብ፣ ማሰቃየትና ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ነገር መፈፀም የለበትም። ከድብደባው ስቃይ ለማምለጥ ሲል ያልፈፀመውን ወንጀል ፈፅሜያለው ቢልስ? ንፁህ ሰው ወንጀለኛ አድርገን ትክክለኛ ወንጀል ፈፃሚዎችን ነፃ ልናደርግ አይደለም ወይ? በድብደባው ምክንያት ሕይወቱን ቢያጣ ወይም በአካሉ ላይ ቋሚና ግዚያዊ ጉዳት ቢደርስበትስ? ለዚህ ችግር ማን ነው ተጠያቂው? ዜጎች በፍትህ ተቋሞቻችን ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይህ ሁሉ ተጠረቃቅሞ ሃገር በህግ የበላይነት ሳይሆን በሰዎች የበላይነት እንድትመራ ያደርጋል። የወገን አለኝታ የሆኑ ተቋሞች እንዳይኖሩን ያደርጋል። መዘዙ ብዙ ነው። እናቶቼ ስሙኝማ…የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው አይበጀንም ይቅርብን አልኳቸው። አንደኛዋ እናት፣ “እኛ ይህን ሁሉ ጉድ መች አወቅንና እንደው ዝም ብለን አፋችን ያመጣልንን እናወራለን እንጁ…” እያሉ ..መኪናው ቆመ.. ረዳቱ… መርሳ ወራጅ ሲል.. ሁለቱ እናቶች ለመውረድ እቃቸውን እየሰበሰቡ….”ገምሻራየዋ” በል በደህና ግባ፣ መንገዱ ቀና ይሁንልህ፣ ቤተሰቦችህን በኸይር አግኛቸው ብለው መርቀው..ተሰናብተውኝ ወረዱ። መኪናው ሳይንቀሳቀስ በፊት ድምፄን ከፍ አድርጌ..ማዘር… ስመዎን አልነገሩኝም እኔ ኃይለማርያም እባላለሁ የአንቱስ?…መከናው ተንቀሳቀሰ..”ሃዋ መሃመድ” የሚል ድምፅ ጆሮየ ላይ ደረሰ።
ሃዋ ኑልኝ፣ እድሜዎ ይርዘም አቦ። አሜን።

ምነው እንዲህ እርቃናችንን ቀረን? ልክ ከቋጥኟ ወጥታ ለመብረር እንዳኮበኮበችው ኤሊ ….

በኃይለማርያም ይርጋ
ሰርጌ ራስቶርጎቨ (Sergei P. Rastorguev) የበይነብመረብ ማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ሃሰተኛ ማንነት እና መረጃ(fake account and news) የሚያመርቱ መተግበሪያወችን( bootnets) ስራ ላይ በማዋል ውሸት ስለሚነዙ(ግራ ስለሚያጋቡ)፣ ዳታዎችን በመስርቅ፣ የግንኙነት መስመርን በማወክና በማጨናነቅ እንዳይሰራ (DOs attack) ስለሚፈፀሙ ድብልቅ የመረጃ ወይም የስነ ልቦና ጦርነት (haybrid information warfare) ተንታኝ ነው። ይህ ጦርነት ሃገራችንን(የበለፀጉ ሃገሮችንም ጭምር) እያሸበረ እና ሃገራትን አፅንተው ያቆዩ እሴቶችን በመበጣጠስ ወደ ገደል አፋፍ እየወሰደ ይገኛል። ሰርጌ ስለዚህ ጦርነት ዋና ግብ በሚከተለው መልኩ ጠቅለል አድርጎ በምሳሌ አቅርቦታል። እነሆ።
ከለታት አንድ ቀን አያ ቀበሮ ኤሊን አድኖ ለመብላት አለኝ የሚለውን የአደን ጥበብ ተጠቅሞ በተደጋጋሚ ለመያዝ ቢሞክርም ኤሊ የዋዛ አልነበረችምና ቶሎ ብላ ወደ ጉያዋ(shell) እየገባች አስቸገረችው። እያገላበጠ፣ እያንከባለለ ሞከረ..እሷቴ..ወይ ፍንክች። ከብዙ ማሰላሰል በኌላ ቀበሮ አንድ ሃሳብ መጣለት። ጉያዋን(ቋጥኟን)፣ ሕይወቷን ሙሉ ለሙሉ ሊቀይር በሚችል ዳጎስ ባለ ብር ለመግዛት ጥይቄ አቀረበላት። እሷም ጠባቂ መከታዋን ከሸጠች ምን ብር ቢኖራት እራቁቷን ቀርታ ለአደን ተጋላጭ መሆኑዋን ተረዳችና እምብየው አለች። …ጊዜው ነጎደ። አንድ ቀን በተንጣለለው መስክ ላይ ዘና ብላ ሳር እየነጨች እያለ ዛፍ ላይ በተሰቀለው የቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ ኤሊዎች እራቁታቸውን ክንፍ አውጥተው እየተሳሳቁ በጋራ ሲበሩ ተመለከተች፣ አላመነችም። ባይበሉባዋ አይኑዋን አሸት አሸት አደረገችና እንደገና ተመለከተች፣ ፈዛ ቀረች። ነገሩ እውነት ነው፣ ተደነቀች። ቆይ.. ‘ራቁት መብረር ለደህንነታቸው ስጋት አይሆንም ? እያለች ብቻዋን እያጉረመረመች እያለ አንድ ማስታወቂያ ከቴሌቭዥኑ ውስጥ አስተጋባ፣ “አያ ቀበሮ ከዛሬ ጀምሮ አትክልት ተመጋቢ(vegeterian) መሆናቸውን ገለፁ ” የሚል ነበር። ይህን በሰማች ጊዜ “እስከመቸ ጉያየ ውስጥ ተደብቄ እኖራለሁ፣ እንደ ባልንጀሮቼ ዘና ብየ እንድኖር ይህን ቋጥኝ ከላይቴ ላይ አውልቄ መጣል አለብኝ” እያለች ማሰላሰል ጀመረች። ቀበሮም የኤሊን ምኞትና ፍላጎት ስለተረዳ ” ቋጥኟን በቀላሉ የምትጥልበትን ብልሃት ዘየደ፣ “የሚበሩትን ኤሊዎች” ማስታወቂያ ብዙ ገንዘብ በማውጣት በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን ተደጋግሞ እንዲነገር ማስደረግ። አንድ ቀን ጧት፣ ሰማዩ ብራ በሆነበት..ምስኪን ኤሊ..ሃገር ሰላም ብላ ቋጥኟን፣ ጥላ ከለላዋን፣ ጠባቂዋን ከላይዋ ላይ አውልቃ ጣለች። አያ ቀበሮም ይች ቀን እንደምትመጣ ያውቅ ነበርና በትዕግስት ጠብቆ ህልሙ ተሳካለት።
እኛም እንዲህ ነው የተታለልነው። የተነገረን፣ የተፃፈልን ሁሉ እውነት፣ መና የሚያዘንብልን መስሎን ‘ሆ’ ብለን የተመምነው። ክንንባችንን አውልቀን እራቁታችን የቀረነው። ሰማይ ምድሩ የተቀላቀለብን (reality up side down)፤ የውር ድንብር የምንሄደው። “ይህን ከማይ፣ ከምሰማ ብሞት ይሻላል(death wish)”፣ ማለት ያበዛ ነው። ይህ ዝም ብሎ ባንድ ጀምበር የተከሰት እንዳይመስልህ፣ ልክ የሮሌክስ ሰዓት እና ደቂቃ ቆጣሪዎች ሲዞሩ እንደማናያቸው ሁሉ ክንንባችንን(ጥላ ከለላችንን፣ እሴቶቻችንን) ሳናስተውል፣ ሳይታወቀን አውልቀን እንድንጥል ተደርገናል፤ ከስድሳዎቹ ጀምሮ። ለሃገር የሚበጅ ነገር እየሰራን እየመሰለን ወደ ገደሉ አፋፍ እየገፋናት እዚህ አድርሰናታል።
የዲሞክራሲ ተቋማት መደላድል እንዳይኖርህ እያደረክ፣ የሌሎችን ሃሳብን የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብትን እየነፈግክ (መቼም political correctness ነው አትለኝም) እንዴት ዲሞክራሲ ትጠብቃልህ? ጥላ ከለላየ የምትላቸው የፍትህ ተቋማትን ጥላሸት ቀብተህ እምነት እንዳይጣልባቸው አድርገህ የህግ የበላይነት እንዴት ትጠብቃለህ? የሌሎችን ሃሳብን የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብት እየነፈክ ከሃይማኖት ከህገ ልቦና የሚመነጩ ሰብአዊ ርህራሄ እና ግብረገብነትህን አውልቀህ እንድትጥል ተደርገሃል? በውኑ ታናሽ ታላቁን እንዲያከብር፣ ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባቶች እንዲከበሩ ትሻለህን? የሃገር ጥቅም እና የግለሰብ ጥቅም ተቀላቅሎብናል፣ ስለምንሰራው ስራ ሃላፊነት ወይም ተጠያቂነት እንዳለብን እንኳ ዘንግተናል። መብትና ግዴታችንን መለየት እንዳንችል ተደርገናል። ሃገርን አፅንተው ያኖሩትን ማህበራዊ ፅሴቶች አውልቀህ እንድትጥል ተደርገህ ስለ ሃገር አንድነት ብትሰብክ ምን ዋጋ አለው፣ አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል እንዲል ከያኒው። ሆን ተብሎ በተፈጠረ አጀንዳ ወይም ኩነት (orcastrated event) ሰለባ በመሆን ከመንግስት ጎን መሆን ሲገባህ ምሳር እንደበዛበት ዛፍ መጠጊያ ከለላህን ውርጅብኙን ታወርድበታለህ። በማን እና ለምን ብለህ አትጠይቅም፣ ዝም ብለህ በተከፈተልህ ቦይ መፍሰስ። አለሞቼ አሁንም አልረፈደም።
በተቻላችሁ አቅም የጋራ የሞራል እሴቶቻችሁን ጠብቁ(stay moral) ቢያንስ አስርቱ ትዕዛዛትን አክብሩ፣ ጠብቁ። አፍራሾችን አትተባበሩ፣ አትርዱ(don’t click read more, like and share)፣ ሚዲያቸውን፣ ግዜጦቻቸውን አታንብቡ አትከታተሉ። ቢያንስ የኢንተርኔት አልጎሪዝም ሰለባ ሆናችሁ፣ የገደል ማሚቶ ከመሆን ትድናላችሁ(ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)። የሃገር አንድነትና አብሮነት የሚሰብኩ ተቋማትንና ሚዲያወችን ደግፉ፣ መልዕክቶቻቸው ሌሎች እንዲደርሳቸው አግዙ።
ምነው እንደኤሊዋ እራቁቴን ካልበረኩ አላችሁ፣ አበስኩ ገበርኩ😀

አስተያየታችሁን አቀብሉን hihoney3@gmail.com

የፖለቲካ ገለልተኝነት ዐቃቤ ሕግ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም

በዘሪሁን ሽፈራው
e-mail: zerihunshiferaw490@gmail.com

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፷፪/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፷፫ የፖለቲካ ፓርቲ ስለ መመስረት ያትታል፡፡
ይህ አንቀጽ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት መኖሩን እንዲሁም ማንኛውም እድሜው ከ፲፰ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት የአገር አቀፍ ወይም የክልል የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት እንዳለው ያስረዳል፡፡
ይህ ጠቅላላ ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጉ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ክልከላ ያስቀመጠባቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በዚህ ዝርዝር የሚገኙ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባል፣ የፖሊስ፣ የደህንነት እና የጸጥታ አካላት ሰራተኛ እና የምርጫ ቦርዱ ባለስልጣናት እና ሰራተኞች ናቸው፡፡
ሁለት ወዶ አይቻልምና እነኝህ ሥራችሁን ብቻ ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ግዴታ የተጣለባቸው ሰዎች በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመንቀሳቀስ ከፈለጉ የመንግሥት ስራቸውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ይህ ሀሳብ በግልጽ በአዋጁ አንቀጽ አንቀጽ ፷፫(፬) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ገደቡን በማለፍ ሥራዉን ሳይለቅ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ያለመሆን ድንጋጌውን በመጣስ በፖለቲካ የሚሳተፊ ግለሰብ ከያዘው የመንግሥት ሥራ በራሱ ፈቃድ እንደለቀቀ ተቆጥሮ በሚመለከተው አካል አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል፡፡
በዚህ ምርጫ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያለመሆን ግዴታ ከተጣለባቸው ሥራ ዘርፎች የዐቃቤ ሕግ ሥራን በተመለከተ ከዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ ሕጎች እና መተዳደሪያ ደንቦች አንጻር በመመርመር መሠረታዊ የሕግ አተረጓገም መርህ አንጻር ሁሉም ዐቃቤ ሕግ ከፖለቲካ አባልነት ነጻ የመሆን ግዴታ አለበት ወይስ አይደለም በሚለው ክርክር ልያስነሳ በሚችል ሀሳብ ላይ የሚከተለው መደምደሚያ መስጠት ይቻላል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፱፻፵፫/፪ሺ፰ ዓ.ም አንቀጽ ፪ (፰) “ዓቃቤ ሕግ” ማለት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተሹሞ በዓቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የሚተዳደር የሕግ ባለሙያ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፯ (፩) መሠረት የተሾሙ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንና ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤያነ ሕግን ይጨምራል በማለት ትጉም ይሰጣል፡፡ ይህንን ትርጉም እስከ ሥር መዋቅር ባሉ ኃላፊዎች በማዳረስ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር ፻፸፯/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፪(፲፪) “ዓቃቤ ሕግ” ማለት በመስተዳድር ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት የሚቀጠር ወይም የሚመደብ እና የሚተዳደር የሕግ ባለሙያ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፯ መሠረት የተሾሙ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን፣ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤያነ ሕግን እና በየእርከኑ ያሉት የዓቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችንም ይጨምራል በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ዐቃብያነ-ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር ፻፸/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፷፪ ስለ ዐቃቤ ሕግ ገለልተኝነት ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ማንኛዉም ዐቃቤ ህግ በፖለቲካ እንቅስቃሰ መሳተፍ ወይም አባል መሆን ወይም አመለካከቱን በስራ ላይ መግለፅ ወይም በማናቸዉም መንገድ ማሳየት የተከለከለ ነዉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፪(፪) የተሰጠው የዐቃቤ ሕግ ትርጉም የተቋሙ ኃላፊዎችንና ምክትሎችን እንዲሁም በየደረጃው እስከ ሥር መዋቅር የሚመዘረጋውን ካላይ ካየናቸው ሕጎች በተለየ መልኩ ነው የሚተረጉመው፡፡ ይህ ደንብ “ዓቃቤ-ሕግ” ማለት በዚህ ደንብ አንቀጽ ፮ ከተመለከተው የስራ ደረጃ ዝርዝር በአንዱ የተቀጠረ ወይም የተመደበ ሰው ነው በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡ ዝርዝሩ የሚያካትተው ከተቋሙ ኃላፊና ምክትሎች ውጭ ያሉትን ዐቃቤ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ካየናቸዉ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ፣ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጆች እና ዐቃብያነ-ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ስለዐቃቤ ሕግ የተደነገጉ ሀሳቦችን ስንመለከት የምርጫ አዋጁ ያስቀመጠው ክልከላ መተግበር ያለባቸዉ የትኛው ዐቃቤ ሕግ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመሥጠት የዐቃቤ ሕግ ትርጉም ስንፈልግ የዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እና መተዳደሪያ ደንብ የተለያየ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ በሕግ ተዋረድ/hierarchy of law/ ደንብ ከአዋጅ ዝቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ደንብ አዋጅ በጥቅል የሚያስቀመጣቸዉን ሀሳብ በዝርዝር በማብራራት ለአፈጻጸም እንዲመች ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ የሰጣቸዉን መብት የማጣበብ እንዲሁም ትርጉም መቀነስ አቅም አይኖረዉም፡፡ ከዚህ መርህ አንጻር ከላይ ባየነዉ ደንብ ለዐቃቤ ሕግ የተሰጠው ትርጉም ከአዋጁ የሚጻረር በመሆኑ የደንቡ ትጉም ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ ማለት በትክለኛ የሕግ አተረጓገም ሥርዓት ከፖለትካ ወገንተኝነት ነጻ የመሆን ግዴታ የዐቃቤ ሕግ ባለሙያዎች እና የተቋሙ መሪዎች ጭምር ነው ማለት ነው፡፡
ማን ያውቃል የተቋሙ ኃላፊ መሆን የሚገባው የፖለቲካ ተሿሚ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ ተቋም አንዱ የአስፈጻሚ ተቋም ነው ስለዚህ ይህንን ተቋም መምራት ያለበት በፖለቲካ ታማኝነት ያለው የገዥ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው መሆን አለበት የሚል አቋም ያላቸዉ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ከላይ ላስቀመጥኩት መደሚደሚያ መነሻ ያረኩት እነኝህን ምክንያቶች ሳይሆን የሕግ አተረጓገም መርህ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡
ከዚህም ባሻገር ዐቃቤ ሕግ ተቋም ከአስፈጻሚ ተቋማት ውጭ የሆነ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም ተደርጎ የሚጣይባቸዉ ሀገራት እንዳሉ በሀገራችንም በደርግ ዘመን ልዩ ዐቃቤ ሕግ በሚል ከሌሎች አስፈጻሚ ተቋማት በተለየ መልኩ ተዋቅሮ እንደነበረ የሚያሳዩት ዐቃቤ ሕግ ተቋም ከሌሎች አስፈጻሚዎች ለይተዉ ከፖለቲካ ገለልተኛ በሆነ መልኩ ማዋቀር እንደሚቻል ማሳያ ልሆን ይችላል፡፡ የፍትህ ተቋማት ከሚባሉት አንጋፋዉ ፍርድ ቤት ከፖለትካ ገለልተኛ በሆነ ዳኛ/ፕረዚዳንት/ መመራቱ በማሕበረሰቡ ዘንድ ለፍትህ ያለውን አመለካከት ከፍ ማድረጉ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ የዚህንም አምሳል /analogy/ ለዐቃቤ ሕግ ተቋም መጠቀም ይቻላል፡፡
በመሆኑም የሕዝብ ተአማኒነት ያለው፣ በተሟላ ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነት የሚያገለግል እንዲሁም ለሙያዊ፣ ተቋማዊና ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሚገዛ፣ በግልጽነትና አሳታፊነት የሚሰራ የዓቃቤ ሕግ ተቋም የማደራጀት ዐላማ ይዞ በተቋቋመዉ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ዐላማዉን ወደ ግብ ለማድረስ ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የተቋሙ መሪዎቹንም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሚያደርግ አሠራር ልኖር እንደሚገባ እንዲሁም በአዋጅ የተሰጠዉን ትርጉም ደንብ ዋጋ ማሳጣት ስለማይችል የአዋጁን ትርጉም በመተግበር ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የተቋሙ ኃላፊዎችንም ገለልተኛ በማድረግ ለፍትህ የቆሜ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም እዉን መደረግ አለበት እላለሁ፡፡78850670_2519381988350688_6360868684457574400_o

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ እና የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁ.1162/2011 እዚህ ያውርዱ

click the link below to download the two document

AMHARIC TERRERISM DRAFT PROCLAMATION for HOPR-2

1162-2019_Gztd የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁ.1162/2011የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁ.1162/2011

የተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ ዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ……/2011

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ

ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በማስያዝ ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ካፒታል ማግኘት እንዲችሉና በሂደቱም የፋይናንስ ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት የሚያስችል በመሆኑ
ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ ብድር ማግኘት የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋትና የማስፈጸሚያ መንገዱንም ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤
ለዋስትና በተያዘ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በተወዳዳሪ ባለመብቶች የሚነሳ የቀዳሚነት መብትን ለመወሰን የሚያስችል አንድ ወጥና ሁሉንአቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ስለሆነ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55/1/መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ ‹‹የተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ ቁጥር…./ 2011›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ የተለየ ትርጓሜ የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፤
1/ ‹‹የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ›› ማለት ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተያያዘ ቢሆንም እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የሚቆጠር ሀብት ነው፤
2/ ‹‹የተገኘ የዋስትና መብት›› ማለት በግዑዝ ሀብት ወይም አዕምሯዊ ንብረት ላይ ያልተከፈለ ቀሪ ዋጋን ለማስፈጸም ወይም መያዣ ሰጪው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ ለማድረግ የተፈፀመ ብድርን ለማስከፈል እንዲቻል በዚያው መጠን በንብረቱ ላይ የተገኘ የዋስትና መብት ነው፤
3/ ‹‹የንግድ ተቋም›› ማለት በንግድ ሕግ የተመለከተው የንግድ መደብር ነው፤
4/ ‹‹በሰነድ የተደገፈ ሴኩሪቲ›› ማለት ሰነዱን በያዘው ሰው ስም ወይም ለአምጪው ተብሎ የታዘዘ አክሲዮን ወይም ቦንድ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ነው፤
5/ ‹‹የመያዣ መዝገብ›› ማለት በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በስምምነት ወይም ከህግ ወይም ከፍርድ የመነጨ የዋስትና መብት መረጃን መቀበያ፣ ማስቀመጫ እና ለሕዝብ ተደራሽ ማድረጊያ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ነው፤
6/ ‹‹የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት›› ማለት የመያዣ ምዝገባ ሥርዓትን ለማስተዳደር የሚቋቋም ጽህፈት ቤት ነው፤
7/ ‹‹ተወዳዳሪ ባለመብት›› ማለት ገንዘብ ጠያቂ ወይም በዋስትና በተያዘ ንብረት ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ጋር ተወዳዳሪ የመብት ጥያቄ ያለው ሌላ ሰው ነው፤
8/ ‹‹የፍጆታ ዕቃዎች›› ማለት መያዣ ሰጪው በዋናነት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ የቤት ውስጥ ፍጆታ የሚጠቀምባቸው ወይም ለመጠቀም ያዘጋጃቸው ዕቃዎች ናቸው፤
9/ ‹‹የቁጥጥር ስምምነት›› ማለት፣
ሀ) የኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ዋስትናን በተመለከተ በሰነዱ አውጪ፣ በመያዣ ሰጪው እና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል የተደረገና አውጪው የመያዣ ሰጪው ተጨማሪ ፈቃድ ሳያስፈልገው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በቀጥታ የሚፈጽምበት የጽሑፍ ስምምነት ነው፡፡ ወይም
ለ) ከተቀማጭ ሂሳብ ላይ ክፍያ የማግኘት መብትን ለማስፈጸም በፋይናንስ ተቋሙ፣ በመያዣ ሰጪው እና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል የተደረገና የፋይናንስ ተቋሙ የመያዣ ሰጪው ተጨማሪ ፈቃድ ሳያስፈልገው በመያዣ ሰጪው ሂሳብ ውስጥ በተቀመጠ ገንዘብ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በቀጥታ የሚፈጽምበት የጽሑፍ ስምምነት ነው፤
10/ ‹‹ግዑዝ ሀብት›› ማለት ገንዘብ፣ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ፣ የሚተላለፍ ሰነድ እና በሰነድ የተደገፉ ሴኩሪቲዎችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ነው፤
11/ ‹‹ባለዕዳ›› ማለት ዋስትና ለተገባለት ግዴታ ገንዘብ የመክፈል ወይም ግዴታውን የመፈጸም ኃላፊነት ያለበት ሰው ሲሆን ለዚሁ ዋስ የሆነንም ይጨምራል፤
12/ ‹‹የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ›› ማለት የተሰብሳቢ ሂሳብን የመክፈል ግዴታ ያለበት ሰው ሲሆን፣ ለሂሳቡ ክፍያ ዋስ የሆነን ወይም በሁለተኛ ደረጃ ዋስ የሆነ ሌላ ሰውን ይጨምራል፤
13/ ‹‹ተቀማጭ ሂሳብ›› ማለት ከሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ ፈቃድ በተሰጠው የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ያለ ሂሳብ ነው፤
14/ ‹‹መሣሪያ›› ማለት ከንግድና የፍጆታ ዕቃዎች ውጭ የሆነና መያዣ ሰጪው በዋናነት ለሥራው የሚጠቀምበት ወይም ሊጠቀምበት የያዘው ግዑዝነት ያለው ሀብት ነው፤
15/ ‹‹ኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች›› ማለት ኤሌክትሮኒካዊ በሆነ መንገድ የተመዘገቡ፡ የሚተላለፉ እና በሰነድ ያልተደገፉ አክሲዮኖችና ቦንዶች ናቸው፤
16/ ‹‹የግብርና ምርቶች›› ማለት የበቀሉ ወይም በመብቀል ላይ ያሉ ወይም ወደፊት የሚበቅሉ ሰብሎች፣ ደንና የደን ውጤቶች፣ የቤት እንሰሳት የሚወለዱትን ጨምሮ፣ የንብና የዶሮ ዕርባታ፣ ለግብርና ሥራ ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብአቶች ወይም በግብርና ሥራ የተመረቱ፣ ወይም በምርት ሂደት ያልተቀየሩ የሰብል ወይም የእንስሳት ምርቶችንና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ያጠቃልላል፤
17/ ‹‹የፋይናንስ ኪራይ›› ማለት አከራዩ አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን በተከራዩ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ በሁለቱ ወገኖች ስምምነት የተወሰነ ክፍያ በየተወሰነ ጊዜ በመፈጸም እንዲጠቀምበት የሚያከራይበት፣ የኪራይ ስምምነቱ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ አከራዩ በካፒታል ዕቃው ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት ይዞ የሚቆይበትና የኪራይ ዘመኑ ሲያበቃ ሁለቱም ወገኖች ከተስማሙ ተከራዩ የካፒታል ዕቃውን ሊገዛ የሚችልበት የኪራይ ዓይነት ነው፤
18/ ‹‹ታሳቢ ሀብት›› ማለት ገና ያልተፈጠረ ወይም የዋስትና ስምምነቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መያዣ ሰጪው ገና የባለቤትነት መብት ያላገኘበት ተ ንቀሳቃሽ ንብረት ነው፤
19/ ‹‹መያዣ ሰጪ›› ማለት ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ግዴታ ማስፈፀሚያ ዋስትና ያስያዘ፣ በዋስትና ግዴታ የተያዘ ንብረትን ከነግዴታው የገዛ፣ የተላለፈለት፣ የተከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ያለው፣ በዱቤ ግዢ መሠረት የተከራየ ሰው ነው፤
20/ ‹‹የዱቤ ግዢ›› ማለት አከራይና ተከራይ ባደረጉት ስምምነት መሠረት አከራይ በተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ክፍያ እየተከፈለው አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን ተከራዩ እንዲጠቀምበት የሚፈቅድበት፣ እያንዳንዱ ክፍያ በተደረገ ቁጥር ለክፍያው ተመጣጣኝ በሆነ መቶኛ ልክ ለተከራይ የባለቤትነት መብት የሚተላለፍበትና ተከራይ የመጨረሻውን ክፍያ እንደፈጸመም በካፒታል ዕቃው ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት ወዲያውኑ የሚያገኝበት የኪራይ ዓይነት ነው፤
21/ ‹‹ግዑዝነት የሌለው ሀብት›› ማለት ተሰብሳቢ ሂሳብን፣ ተቀማጭ ሂሳብን፣ የአእምሯዊ ንብረት መብትንና ከግዑዝ ንብረት ውጭ ያሉ ተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ያካትታል፤
22/ ‹‹አዕምሯዊ ንብረት›› በአገሪቱ አእምሯዊ ንብረት ህጎች የተሰጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡
23/ ‹‹የንግድ ዕቃ›› ማለት ጥሬ እና በከፊል የተቀነባበሩትን ጨምሮ መያዣ ሰጪው በመደበኛ የንግድ ሥራ ሒደት ለሽያጭ ወይም ለኪራይ የያዘው ግዑዝ ሀብት ነው፤
24/ ‹‹ውህድ ወይም ምርት›› ማለት አንድን ምርት ከሌላ ምርት ጋር በማዋሀድ ወይም በመቀላቀል የሚፈጠር አዲስ ይዘት ያለው ምርት ወይም ውህድ ነው፤
25/ ‹‹ገንዘብ›› ማለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚታተሙ ሕጋዊ መገበያያ የገንዘብ ኖቶች እና የሚቀረጹ ሳንቲሞች፣ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጸም ክፍያ ተቀባይነት ያላቸውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገለጹ የሌላ ሀገር ሕጋዊ የመገበያያ የገንዘብ ኖቶች እና ሳንቲሞች ናቸው፤
26/ ‹‹ተንቀሳቃሽ ንብረት›› ማለት የንግድ ዕቃዎችን፣ የግብርና ምርቶችን፣ ግዑዝነት የሌላቸው ሀብቶችን፣ ግዑዝ ሀብቶችን፣ ከመሬት፣ ከቤት ወይም ከሕንጻ ውጭ ያሉ ንብረቶችን፣ በሕግ ካልተከለከለ በስተቀር በመሬት ላይ የመጠቀም መብትን፣ በዱቤ ግዢ የሚገኝ መብት፣ በአደራ የተቀመጠ ንብረት ሠነድ፣ የአደራ መያዣ ደረሰኝ፣ የሸቀጦች ጭነት፣ ንግድን ለዋስትና ማስያዝ፣ ባለቤትነትን በማስጠበቅ የሚደረግ ሽያጭ፣ የተሸጠ ንብረትን መልሶ ለመግዛት መብት የሚሰጥ ሽያጭ፣ በምስክር ወረቀት የሚረጋገጡ ሴኩሪቲዎች ላይ የሚመሠረት የዋስትና መብት፣ እና በመጋዘን ደረሰኝ ላይ ያለ የዋስትና መብትን ያካትታል፤
27/ ‹‹የሚተላለፍ ሰነድ›› ማለት በሰነዱ ላይ የተገለጸውን ንብረት የመረከብ መብት የሚሰጥና ሊተላለፍ የሚችል እንደ ማጓጓዣ ሰነድ፣ ቫውቸር ወይም በመጋዘን የተቀመጠ ዕቃ መቀበያ ደረሰኝ ነው፤
28/ ‹‹የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ›› ማለት የሐዋላ ወረቀት፣ የተስፋ ሰነድ እና ከቼክ በስተቀር ሌላ ለአምጪው ወይም በስሙ ወይም ለታዘዘለት ተብሎ የተዘጋጀ ሰነድን ያካትታል፤
29/ ‹‹በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ›› ማለት በዋስትና መያዣ ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም በሕግ ገንዘብ የመጠየቅ መብት ያገኘ ሰው ነው፤
30/ ‹‹ማስታወቂያ›› ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ወይም ፈቃድ በተሰጠው ሰው በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የሚካተት የመጀመሪያ ምዝገባ፣ የማስተካከያ ምዝገባ ወይም የስረዛ ምዝገባ ነው፤
31/ ‹‹የአጭር ጊዜ መጠቀሚያ ኪራይ›› ማለት በአከራዩ እጅ የሚገኝ አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን ተከራዩ በሁለቱ ወገኖች ስምምነት የተወሰነ ኪራይ በመክፈል ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲጠቀምበት የሚከራይበት የኪራይ ዓይነት ነው፤
32/ ‹‹ቀደምት ሕግ›› ማለት ይህ አዋጅ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በሥራ ላይ የነበረ ሕግ ነው፤
33/ ‹‹ቀደምት የዋስትና መብት›› ማለት ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት በተፈጸመ የዋስትና ስምምነት የተሸፈነ መብት ነው፤
34/ ‹‹ይዞታ›› ማለት አንድ ሰው ወይም ተወካዩ አንድን ግዑዝ ንብረት በራሱ ወይም በሌላ ሰው ሃላፊነት ሥር እንዲሆን ማድረግ ነው፤
35/ ‹‹ተያያዥ ገቢ›› ማለት ከዋስትና መያዣው የሚገኝ ማንኛውም ገቢ ሲሆን፣ በሽያጭ፣ በማስተላለፍ፣ በመሰብሰብ፣ በማከራየት ወይም በፈቃድ የተገኘ ወይም የፍሬ ገቢ፣ የመድን ገቢ፣ በዋስትና ከተያዘው ንብረት ብልሽት፣ ጉዳት ወይም መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚሰበሰብ ገቢንና በዚሁ ገቢ አማካይነት የተገኘ ተጨማሪ ገቢን ያካትታል፤
36/ ‹‹ተሰብሳቢ ሂሳብ›› ማለት ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆን ከሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ፣ ከተቀማጭ ሂሳብ እና ከዋስትና የሚገኝ የክፍያ መብትን ሳይጨምር ገንዘብ የመከፈል መብት ነው፤
37/ ‹‹የታወቀ ገበያ›› ማለት ዋጋ በይፋ የሚገለጽበት እና/ወይም በንግድ አሰራር ተገቢ ነው ተብሎ የሚታመንበት የተለመደና የታወቀ ገበያ ማለት ነው፤
38/ ‹‹መዝጋቢ›› ማለት ምዝገባው በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት መረጃዎችን በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የሚመዘግብ ወይም የሚያካትት ሰው ነው፤
39/ ‹‹ሬጅስትራር›› ማለት የመያዣ ምዝገባ ሥርዓቱን እንዲያስተዳድር እና እንዲቆጣጠር በመንግስት የሚሾም ሰው ነው፤
40/ ‹‹መረጃ›› ማለት በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የተቀመጠ፣ የተጠበቀ፣ የተደራጀና ለሕዝብ ክፍት የሆነ የተመዘገበ መረጃ ነው፤
41/ ‹‹ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ›› ማለት የዋስትና መብት ያለው ወይም በህግ ወይም በፍርድ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው ነው፤
42/ ‹‹የዋስትና ስምምነት›› ማለት ተዋዋይ ወገኖች የዋስትና ስምምነት ብለው ባይሰይሙትም በመያዣ ሰጪውና በመያዣ ተቀባዩ መካከል የተፈረመ የዋስትና መብት የሚፈጥር ስምምነት ነው፤
43/ ‹‹የዋስትና መብት›› ማለት ተዋዋይ ወገኖች የዋስትና መብት ብለው ባይሰይሙትም በንብረቱ ዓይነት፣ በመያዣ ሰጪውና ተቀባዩ እና ዋስትና በተገባለት ግዴታ ላይ ሳይወሰን የክፍያ ወይም ሌላ ግዴታን ለማስፈጸም በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚፈጠር መብት ነው፤
44/ ‹‹መለያ ቁጥር›› ማለት በሻሲ ወይም በሌላ የፋብሪካ ምርት አካል ላይ የሚገኝ መለያ ቁጥር ነው፤
45/ ‹‹መለያ ቁጥር ያለው መያዣ›› ማለት በአምራቹ በቋሚነት የተጻፈ ወይም የተለጠፈ መለያ ቁጥር ያለው ሞተር ተሽከርካሪ፣ ተሳቢ፣ የእርሻ መሣሪያ፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያ፣ የኢንዱስትሪ መሣሪያ እና ሌላ መለያ ቁጥር ያለው ዕቃ ነው፤
46/ ‹‹ሰው›› ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤
47/ ማንኛውም በወንድ ጾታ የተገለፀው የሴትንም ያካትታል
3. የተፈፃሚነት ወሰን
1/ ይህ አዋጅ የግብይቱ ዓይነት፣ የተንቀሳቃሽ ንብረቱ ዓይነት፣ መያዣ ሰጪው ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ሁኔታ ወይም ዋስትናው የተጠበቀለት ግዴታ ባህርይ ከግምት ውስጥ ሳይገባ፣ የክፍያ ወይም ሌላ ግዴታ አፈጻጸም በስምምነት በሚመሠረቱ በሁሉም ተንቀሳቃሽ ንብረት መብቶች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
2/ ይህ አዋጅ
ሀ) በገበያ የሚሸጡ ሴኩሪቲዎች ላይ የሚመሰረት የዋስትና መብት ላይ፣
ለ) የባሕር ሕግ ተፈፃሚ የሆነበት መርከብና ለአገልግሎቱ የሚውሉ ተጓዳኞች ላይ የሚመሰረት የዋስትና መብት ላይ፣
ሐ) በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በተመዘገበ አውሮፕላን ላይ የሚገኝ የተጠቃሚነት መብት ላይ፣
መ) በዚህ አዋጅ ካልተገለፀ በስተቀር ብድር እስኪመለስ ድረስ ገንዘብ ጠያቂው በሕግ እንዲይዘው በተፈቀደ ንብረት ላይ፣ እና
ረ) አንድ ተያያዥ ገቢ ከዚህ አዋጅ የተፈፃሚነት ወሰን ውጭ ከሆነ፣ በገቢው ላይ ሌሎች ሕጎች ተፈጻሚነት ካላቸውና የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎችን የሚሸፍኑና የሚፈቅዱ ከሆነ፣ ይህ አዋጅ በተያያዥ ገቢው የዋስትና መብት ላይ፣
ተፈፃሚ አይሆንም፤
3/ ይህ አዋጅ በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሕግ መሠረት በማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ ላይ የሚፈጠር ዋስትናን አይከለክልም፡፡

ክፍል ሁለት
የዋስትና መብት አመሠራረት

4. የዋስትና መብት በስምምነት የሚመሠረት ስለመሆኑና ይዘቱ
1/ የዋስትና መብት የሚመሠረተው በስምምነት ሆኖ መያዣ ሰጪው ለዋስትና ባቀረበው ንብረት ላይ የባለቤትነት ወይም የማስያዝ መብት ሊኖረው ይገባል፡፡
2/ በዱቤ ግዢ ውል መሠረት በተገኘ የካፒታል ዕቃ ላይ ተከራይ የዋስትና መብት መፍጠር ይችላል፡፡ ሆኖም የመብቱ ከፍተኛ መጠን ከዕቃው ዋጋ ላይ ለአከራይ ሊከፈል የሚገባው ቀሪ ዕዳ ተቀንሶ በሚቀረው መጠን ላይ ብቻ የተወሰነ ይሆናል፡፡
3/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም የዋስትና መብት ስምምነት በታሳቢ ሀብት ላይ መመስረት ይቻላል፡፡
4/ የዋስትና መብት ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝን በመያዣነት ሊይዝ ይችላል፡፡ ሆኖም ተጓዳኙ ከተንቀሳቃሹ ወይም ከማይንቀሳቀስው ንብረት ጋር በአካል መያያዙ መብቱን ቀሪ አያደርግም፡፡
5/ የዋስትና ስምምነት በጽሑፍ የተደገፈና በመያዣ ሰጪው ፊርማ የተረጋገጠ ሆኖ፣
ሀ) የመያዣ ሰጪውንና የዋስትና ተቀባዩን ማንነት፡
ለ) ዋስትና የተገባለትን ግዴታ፣ እና
ሐ) በዚህ አዋጅ አንቀፅ 6 መሠረት መያዣውን፣
መግለጽ ይኖርበታል፡፡
5. ዋስትናቸው ሊጠበቅ የሚችል ግዴታዎች
አንድ የዋስትና መብት የታወቀ ወይም ታሳቢ የሆነ፣ የተረጋገጠ ወይም ሊረጋገጥ የሚችል፣ በቅድመ ሁኔታ ወይም ያለ ቅድመ ሁኔታ፣ የተቆረጠ ወይም ተለዋዋጭ የሆነ አንድ ወይም ከአንድ በላይ ግዴታዎችን ሊሸፍን ይችላል፡፡
6. የመያዣው እና የዋስትናው ግዴታ መግለጫ
1/ መያዣው እና የዋስትናው ግዴታ በዋስትና ስምምነቱ ውስጥ በበቂ ሁኔታና በግልጽ ሊለዩ በሚያስችል መልኩ ሊገለጹ ይገባል፡፡
2/ መግለጫው የዋስትና መያዣውን በዝርዝር፣ በምድብ፣ በዓይነት፣ ወይም በብዛት በመለየት ማስቀመጥ አለበት፡፡
3/ ዋስትናው የተጠበቀ ግዴታ አሁን የተገባ ወይም ወደፊት የሚገባ ተብሎ፣ በአንድ ጠቅላላ ምድብ ወይም እያንዳንዱ ተለይቶ እና ዋስትና የተገባለትን ግዴታ ከፍተኛ መጠን በማመልከት መገለጽ ይኖርበታል፡፡
7. በተያያዥ ገቢ ላይ ስለሚኖር መብት
1/ በአንድ ሀብት ላይ ያለ የዋስትና መብት በሀብቱ ላይ ተለይተው ሊታወቁ የሚችሉ ተያያዥ ገቢዎችን ያካትታል፡፡
2/ ተያያዥ ገቢ በተቀማጭ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ከተደረገ ወይም ከሌላ ገንዘብ ጋር ከተቀላቀለ፣
ሀ) የተቀላቀለው ገንዘብ ተለይቶ መታወቁ ቢያከትምም የዋስትና መብቱ የተቀላቀለውን ተያያዥ ገቢ ይከተላል፤
ለ) በውህድ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት ንብረቶቹ ከመዋሀዳቸው በፊት በነበረው ተያያዥ ገቢ መጠን ላይ ይገደባል፤
ሐ) ከውህደት በኋላ በማንኛውም ጊዜ የተዋሀደው ገንዘብ ከውህደቱ በፊት ከተቀላቀለው ተያያዥ ገቢ ያነስ ከሆነ፣ በተዋሀደው ገንዝብ ላይ ያለ የዋስትና መብት ጥያቄው በቀረበበት ወቅት በሚኖረው መጠን ላይ የተገደበ ይሆናል፡፡
8. ውህድ ወይም ምርት ውስጥ የተቀላቀሉ ግዑዝ ሃብቶች
ግዑዝ ሀብት ከሌላ ተመሳሳይ ሀብት ወይም ምርት ጋር ቢዋሀድ እንኳን በሃብቱ ላይ የተመሠረተው የዋስትና መብት ወደ ውህድ ወይም ምርቱ ይተላለፋል፡፡
9. የዋስትና መብት እንዳይመሠረት የሚገድቡ ስምምነቶች
1/ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የዋስትና መብት መመሥረትን የሚገድብ ስምምነት በባለመብቱና በባለዕዳው መካከል ቢኖርም ከዚህ በተቃራኒ በመያዣ ሰጪውና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል የተፈጠረ የዋስትና መብት ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም መያዣ ሰጪው በንዑስ አንቀጹ የተመለከተውን ውል በመጣሱ ምክንያት ካለበት ግዴታና ኃላፊነት ነጻ ሊሆን አይችልም፡፡ ሆኖም ሌላኛው ተዋዋይ ወገን፣
ሀ) ለተሰብሳቢ ሂሳቡ ወይም ለዋስትና ስምምነቱ መነሻ የሆነው ውል ተጥሷል በሚል ምክንያት ብቻ ውሉን መተው፣ ወይም
ለ) በውሉ አለመከበር ምክንያት በመያዣ ሰጪው ላይ ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውንም መብት ዋስትና ካለው ገንዘብ ጠያቂ ላይ ማንሳት አይችልም፡፡
3/ ይህ አንቀጽ ተፈፃሚ የሚሆነው፣
ሀ) ከፋይናንስ አገልግሎት በስተቀር ከዕቃ ወይም ከአገልግሎት አቅርቦት ወይም ኪራይ ውል፣
ለ) ከግንባታ ውል ወይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ወይም ኪራይ ውል፣ እና
ሐ) ከአዕምሯዊ ንብረት ሽያጭ፣ ኪራይ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ውል፣
በሚመነጩ ተሰብሳቢ ሂሳቦች ላይ ብቻ ነው፡፡
4/ መያዣ ሰጪው በተቀማጭ ሂሣብ ላይ የዋስትና መብት የመፍጠር መብቱን በማንኛውም ሁኔታ የሚገድብ ውል ከፋይናንስ ድርጅት ጋር ቢዋዋልም እንኳን በተቀማጭ ሂሳቡ ውስጥ ገቢ ከተደረገ ገንዘብ ላይ ክፍያ የማግኘት የዋስትና መብት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
10. ክፍያ ወይም ሌላ ግዴታን ለማስፈጸም ዋስትና ወይም ደጋፊ ስለሚሆኑ ግላዊ ወይም የንብረት መብቶች
1/ ግዑዝነት በሌለው ሀብት ወይም በተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ዋስትናውን በአዲስ ስምምነት ማስተላለፍ ሳያስፈልግ ለክፍያ ወይም ለሌላ ግዴታ አፈጻጸም መጠቀም ይችላል፡፡
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተገለጸው መብት ሊተላለፍ የሚችለው በሌላ አዲስ ስምምነት ከሆነ መያዣ ሰጪው ይህን የተጠቃሚነት መብት ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ የማስተላለፍ ግዴታ ይኖርበታል፡፡
11. በተላላፊ ሰነዶች የተሸፈኑ ግዑዝ ሀብቶች
በተላላፊ ሰነድ ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት በሰነዱ በተካተተ ግዑዝ ሀብት ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
12. ከአዕምሯዊ ንብረት መብት ጋር ስለተያያዙ ግዑዝ ሀብቶች
በአዕምሯዊ ንብረት መነሻነት በተፈጠረ ግዑዝ ሀብት ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት አዕምሯዊ ንብረቱን አያካትትም፤ በአዕምሯዊው ንብረት ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብትም ግዑዝ ሀብቱን አይሸፍንም፡፡
ክፍል ሦስት
የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ስላለው ተፈፃሚነት
13. የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ የሚሆንባቸው መንገዶች
በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሚሆነው፣
1/ የዋስትና መብቱን አስመልክቶ በዋስትና መዝገብ ውስጥ ማስታወቂያው ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ከተመዘገበ፣
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ገንዘብ፣ ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች፣ ተላላፊ ሰነዶችና በሰነድ የተደገፉ ሴኩሪቲዎች በአንቀጽ 56 መሠረት በይዞታው ሥር ካደረገ፣ ወይም
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ወደተቀማጭ ሂሳብ ገቢ የሚደረግ ገንዘብ ወይም በኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ዋስትና ላይ የቁጥጥር ስምምነት ካለው፣
ነው፡፡
14. የተያያዥ ገቢ፣ የውሁድ ወይም ምርት የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ስለሚኖረው ተፈፃሚነት
1/ በአንድ ንብረት ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 መሠረት በንብረቱ ተያያዥ ገቢ ላይም በመያዣ ሰጪውና በዋስትና ተቀባይ መካከል ሌላ ተጨማሪ ስምምነት ሳያስፈልግ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆነው ተያያዥ ገቢው ገንዘብ፤ ተሰብሳቢ ሂሣብ፤ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ ከሆነና ወደ ተቀማጭ ሂሣብ ገቢ ከተደረገ ገንዘብ ላይ ክፍያ የማግኘት መብት ካለ ነው፡፡
2/ በአንድ ሀብት ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ከተገለጹት ተያያዥ ገቢዎች በስተቀር በሌሎች ገቢዎች ላይ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 መሠረት የሚፈጠረው የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው፣
ሀ) ገቢዎቹ ከተፈሩ በኋላ ለአሥር የሥራ ቀናት፣ እና
ለ) በገቢዎቹ ላይ ያለ የዋስትና መብት አሥሩ የሥራ ቀናት ከማለቃቸው በፊት አግባብ በሆነው የዋስትና ዓይነት ላይ ተፈፃሚ ከማድረጊያ መንገዶች በአንዱ አማካኝነት የዋስትና መብቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ፣
ነው፡፡
3/ ግዑዝ ሀብቶች ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 8 መሠረት በውህድ ወይም ምርት ላይ ያለተጨማሪ ሁኔታ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
15. በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆኑ የዋስትና መንገዶች ለውጥ
የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሚሆንባቸው መንገዶች ቢለወጡም በለውጡ ሂደት የጊዜ ክፍተት እስከሌለ ድረስ ተፈፃሚነቱ ይቀጥላል፡፡
16. የዋስትና መብትን ስለማስተላለፍ
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዋስትናው ላይ ያለውን የዋስትና መብት በሙሉ ወይም በከፊል ካስተላለፈ ይህንኑ የሚገልጽ የማስተካከያ ማስታወቂያ ማስመዝገብ ይችላል፡፡
2/ የተላለፈ የዋስትና መብት የማስተካከያ ማስታወቂያ በመዝገብ ላይ ቢመዘገብም ባይመዘገብም ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
17. ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ገቢ ከሚደረግ ገንዘብ ላይ ክፍያ የመጠየቅ መብት
ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
1/ የፋይናንስ ተቋሙን ተጠቃሚ የሚያደርግ የዋስትና መብት በመመሥረት፣
2/ የቁጥጥር ስምምነት በመፈረም፣ ወይም
3/ የተቀማጭ ሂሳብን በይዞታ ሥር በማድረግ፣
ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ገቢ ከሚደረግ ገንዘብ ላይ ክፍያ ለማግኘት የሚያስችል የቁጥጥር መብት ይኖረዋል፡፡
18. ተላላፊ ሰነድና በሰነዱ የሚሸፈኑ ግዑዝ ሀብቶች
1/ በተላላፊ ሰነድ ላይ ያለ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ መብቱ በሰነዱ በተሸፈነው ንብረት ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
2/ የተላላፊ ሰነድ ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ይዞታ ሥር ከሆነ የዋስትና መብቱ በሰነዱ በተሸፈኑ ንብረቶችና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
19. ኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች
ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎችን መቆጣጠር የሚችለው፣
1/ የሴኩሪቲዎቹን ይዞታ ለመመዝገብ ሲባል በአውጪው ወይም በወኪሉ በተዘጋጀ መዝገብ ላይ የዋስትና መብቱን መግለጫ በመፃፍ ወይም ዋስትና ያለውን ገንዘብ ጠያቂ ስም በመመዝገብ፣ ወይም
2/ የቁጥጥር ስምምነት በመፈፀም፣
ነው፡፡

ክፍል አራት

የመያዣ መዝገብ

20. የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት መቋቋም
የተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በደንብ ይቋቋማል፡፡
21. የመያዣ መዝገብ መቋቋም
የዋስትና መብትን እና በህግ ወይም በፍርድ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠውን በሚመለከት መረጃ ለመቀበል፣ ለማስቀመጥና ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ያለው የተንቀሳቃሽ ንብረት የመያዣ መዝገብ ይቋቋማል፡፡
22. መያዣ ሰጪው ለዋስትና ምዝገባ የሚሰጠው ፈቃድ
1/ በመያዣ መዝገብ ውስጥ የማሳወቂያ ምዝገባ የሚከናወነው ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ወይም በህጋዊ ወኪሉ ነው፡፡
2/ መያዣ ሰጪው በጽሑፍ ካልፈቀደ በስተቀር የመጀመሪያ የዋስትና መብት ማስታወቂያ ምዝገባ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
3/ መያዣ ሰጪው በጽሑፍ ካልፈቀደ በስተቀር በዋስትና ስምምነት ያልተሸፈነ መያዣን ለመጨመር የሚደረግ የማስታወቂያ ማሻሻያ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡
4/ ተጨማሪ መያዣ ሰጪ የሚሆነው ሰው በጽሑፍ ካልፈቀደ በስተቀር መያዣ ሰጪ ለመጨመር የሚደረግ የማስታወቂያ ማሻሻያ ተፈፃሚነት የለውም፡፡
5/ በጽሑፍ የተደረገ የዋስትና ስምምነት መያዣ ሰጪው ማስታወቂያው እንዲመዘገብ እንደፈቀደ ይቆጠራል፡፡
6/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት የዋስትና ስምምነት ከቀረበ የመያዣ መዝገቡ መያዣ ሰጪው ምዝገባ እንዲደረግ ፈቃድ ስለመስጠቱ ማረጋገጫ አይጠይቅም፡፡
23. ከአንድ በላይ በሆኑ የዋስትና ስምምነቶች ለተመሰረቱ የዋስትና መብቶች አንድ ማስታወቂያ በቂ ስለመሆኑ
አንድ መያዣ ሰጪ ከአንድ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ጋር በተፈራረመው አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ የዋስትና ስምምነት ላይ የተመሰረቱ የዋስትና መብቶችን በአንድ ማስታወቂያ መመዝገብ ይቻላል፡፡
24. ለሕዝብ ተደራሽ ስለማድረግ
1/ ማንኛውም ሰው በመያዣ መዝገቡ ማስታወቂያ ማስገባት የሚችለው በመያዣ መዝገቡ የተጠቃሚነት መለያ ኮድ ካለው እና በመመሪያ በሚወሰነው መሠረት የአገልግሎት ክፍያ ከከፈለ ነው፡፡
2/ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ የሚቀርበው በተጠቃሚ መለያ ኮድ አማካኝነት እና በዚህ ክፍል መሠረት ማስታወቂያውን ለማቅረብ መብት ባለው ሰው አማካኝነት ብቻ ነው፡፡
3/ ማንኛውም ሰው የመረጃ ፍለጋ ቅጽ በሚጠይቀው መሠረት ለመያዣ መዝገቡ የፍለጋ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡
4/ የመያዣ መዝገቡ የተጠየቀውን መረጃ የማይሰጥ ከሆነ የተከለከለበትን ምክንያት ለመዝጋቢው ወይም ለመረጃ ፈላጊው ወዲያውኑ መግለጽ አለበት፡፡
25. የማስታወቂያ ምዝገባ ወይም የመረጃ ጥያቄን ውድቅ ስለማድረግ
1/ የማስታወቂያ ምዝገባ ወይም የመረጃ ፍለጋ መጠየቂያ ቅፅ በሚጠይቀው መሠረትና ቦታ ላይ መሞላት ያለበት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ መረጃ ካልገባ የመያዣ መዝገቡ የማስታወቂያ ምዝገባውን ወይም ፍለጋውን አይቀበልም፡፡
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እንደተደነገገው ካልሆነ በስተቀር የመያዣ መዝገቡ የማስታወቂያ ምዝገባን ወይም የመረጃ ፍለጋ ጥያቄን ውድቅ ማድረግ አይችልም፡፡
3/ የማስታወቂያ ምዝገባ ወይም የመረጃ ፍለጋ ጥያቄ ውድቅ የተደረገ እንደሆነ የመያዣ መዝገቡ ምክንያቱን ለአስመዝጋቢው ወይም ለመረጃ ፈላጊው ወዲያውኑ ያሳውቃል፡፡
26. የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ምርመራ እንዳያደርግ ስለመከልከሉ
የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የማስታወቂያ ምዝገባ ወይም የፍለጋ ጥያቄ ወይም የማስታወቂያ ይዘትን መመርመር አይችልም፡፡
27. ለመጀመሪያ ማስታወቂያ የሚያስፈልጉ መረጃዎች
1/ የመጀመሪያ ማስታወቂያ የሚከተሉትን አግባብነት ባላቸው ቦታዎች የተሞሉ መረጃዎችን መያዝ ይኖርበታል፣
ሀ) በአንቀጽ 28 መሠረት የመያዣ ሰጪውን መለያ ቁጥር እና ሙሉ ስም፤
ለ) በአንቀጽ 29 መሠረት ዋስትና ያለውን ገንዘብ ጠያቂ ወይም የተወካዩን መለያ፤
ሐ) የመያዣ ሰጨውን እና ዋስትና ያለውን ገንዘብ ጠያቂ አድራሻ፤
መ) በአንቀጽ 30 መሠረት መያዣውን የሚያብራራ መግለጫ፤
ሠ) ምዝገባው ፀንቶ የሚቆይበትን ጊዜ፤ እና
ረ) ለስታትስቲካዊ ዓላማ ብቻ እንዲሰበሰብ በመመሪያ የሚወሰን ማንኛውም ሌላ መረጃ፡፡
2/ ከአንድ በላይ መያዣ ሰጪ ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በሚኖርበት ጊዜ መረጃዎች ለእያንዳንዱ መያዣ ሰጪ ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በተናጠል መሞላት ይኖርባቸዋል፡፡
28. የመያዣ ሰጪው መለያ
1/ መያዣ ሰጪው የተፈጥሮ ሰው ከሆነ፣
ሀ) መለያው በመመሪያ የሚወሰን ልዩ የመታወቂያ ቁጥር፤ እና
ለ) ስሙ የኢትዮጵያ ዜግነት ላለው ሰው የፀና ኦፊሴላዊ መታወቂያ ሠነድ ላይ የሰፈረው ስም ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው የተፈጥሮ ሰው በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የፀና ፓስፖርት ላይ የተገለፀው ስም ይሆናል፡፡
2/ መያዣ ሰጪው የሕግ ሰውነት ያለው ከሆነ፡
ሀ) መለያው በመመሪያ የሚወሰን ልዩ የመታወቂያ ቁጥር ፣ እና
ለ) ስሙ በማቋቋሚያ ሰነድ ወይም ሕግ ላይ የሰፈረ ስያሜ ይሆናል፡፡
29. ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መለያ
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የተፈጥሮ ሰው በሚሆንበት ጊዜ መለያው በመመሪያ የሚወሰን የገንዘብ ጠያቂው ወይም የተወካዩ ሙሉ ስም ይሆናል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የሕግ ሰውነት ያለው በሚሆንበት ጊዜ መለያው በመመሪያ የሚወሰን የገንዘብ ጠያቂው ወይም የተወካዩ ስም ይሆናል፡፡
30. የዋስትና መግለጫ
1/ ለዋስትና የዋለ ወይም የሚውል ንብረት ማስታወቂያ ላይ በበቂ ሁኔታ እንዲለይ በሚያስችል መልኩ ተብራርቶ መገለጽ ይኖርበታል፡፡
2/ መግለጫው የመያዣ ሰጪውን ተንቀሳቃሽ ንብረት በሙሉ፣ ወይም በአንድ በተወሰነ ምድብ ውስጥ ያለ ሁሉንም ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚይዝ መሆኑን ከገለጸ፣ ወይም በብዛት ወይም በስሌት ቀመር ካስቀመጠ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መስፈርትን ያሟላ ይሆናል፡፡
3/ በማስታወቂያው ላይ ያለው መግለጫ በዋስትና ስምምነቱ ካለው መግለጫ ጋር አንድ ዓይነት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የማስታወቂያው መግለጫ በዋስትና ስምምነቱ ከተገለጸው የንብረት ዓይነት የሚበልጥ ሆኖ ከተገኘ ማስታወቂያው በትርፍነት በገለጻቸው ንብረቶች ላይ የዋስትና መብቱ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡
4/ በተመዘገበ ማስታወቂያ ውስጥ አንድን ንብረት መጥቀስ መያዣ ሰጪው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንዳለው ወይም ወደፊት እንደሚኖረው አያመላክትም፡፡
5/ የንግድ ዕቃ ካልሆነ በስተቀር መለያ ቁጥር ያለው መያዣ መለያ ቁጥር፣ በዓይነቱና በአምራቹ ስም መገለጽ አለበት፡፡
31. የማስታወቂያ ምዝገባ ተፈፃሚ ስለሚሆንበት ጊዜ
1/ የመያዣ መዝገቡ ለመጀመሪያ ማስታወቂያ ልዩ የምዝገባ ቁጥር በመስጠት እና ይህንን ቁጥር መሠረት በማድረግ የተመዘገቡ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያዎችን መጀመሪያ ከተመዘገበው ማስታወቂያ ጋር ያያይዛል፡፡
2/ የመጀመሪያ፣ የማሻሻያ እና የስረዛ ማስታወቂያ መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ በመያዣ መዝገቡ ከተመዘገቡበት ቀን እና ሰዓት ጀምሮ ለህዝብ ክፍት ይሆናሉ፡፡
3/ የመያዣ መዝገቡ በማስታወቂያው ውስጥ ያለውን መረጃ ማስታወቂያው በቀረበበት ቅደም ተከተል ወዲያውኑ ወደመዝገቡ ያስገባል፡፡
4/ የመያዣ መዝገቡ ለመረጃ ፈላጊዎች ተደራሽ እንዲሆን በማስታወቂያው ውስጥ ያለው መረጃ ወደመዝገቡ የገባበትን ቀን እና ሰዓት ይመዘግባል፡፡
32. የማስታወቂያ ምዝገባ የሚቆይበት ጊዜ
1/ የመጀመሪያ ማስታወቂያ ተፈፃሚ ሆኖ የሚቆይበት ጊዜ መዝጋቢው በማስታወቂያው ላይ ይህንኑ ለማመልከት በተዘጋጀው ቦታ ላይ የገለጸው ሆኖ ከአሥር ዓመት መብለጥ የለበትም፡፡
2/ የመጀመሪያ ማስታወቂያ ምዝገባ የተፈፃሚነት ጊዜ ከማብቃቱ በፊት ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ምዝገባው እንዲራዘም በሚጠይቅብት ቦታ ላይ ከአሥር ዓመት የማይበልጥ የተጨማሪ ጊዜ በመመዝገብ ሊራዘም ይችላል፡፡
3/ የመጀመሪያ ማስታወቂያ የተፈፃሚነት ጊዜ ከአንድ ጊዜ በላይ መራዘም ይችላል፡፡
4/ የጊዜ ማሻሻያ የዋስትናው መራዘም የሚጀምርበትን ቀን ካላስቀመጠ የዋስትናው የተሻሻለው ማስታወቂያ ከሚያበቃበት ቀን ጀምሮ በማስታወቂያው ላይ ለተመለከተው ጊዜ ይራዘማል፡፡
33. የተመዘገበ ማስታወቂያ ግልባጭ የመላክ ግዴታ
1/ አንድ ማስታወቂያ እንደተመዘገበ የመያዣ ምዝገባ ሥርዓቱ ወዲያውኑ ምዝገባው መፈፀሙን የሚገልጽ ሰነድ ለመዝጋቢው የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
2/ ምዝገባው መፈፀሙን የሚገልጸው ሰነድ ምዝገባው የተፈፀመበትን ቀን ፣ ሰዓት፣ እና የምዝገባውን ቁጥር የሚያሳዩ መረጃዎች መያዝ ይኖርበታል፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት መዝጋቢው የማስታወቂያውን ግልባጭ በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ማስታወቂያው ውስጥ በመያዣ ሰጪነት ለተመዘገበው ሰው መላክ ይኖርበታል፡፡
34. የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ የመመዝገብ መብት
1/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) እንደተጠበቀ ሆኖ በተመዘገበ የመጀመሪያ ማስታወቂያ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ተብሎ የተጠቀሰው ሰው ምዝገባውን አስመልክቶ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ መመዝገብ ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ማንነት የሚቀይር የማሻሻያ ማስታወቂያ ከተመዘገበ በኋላ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ መመዝገብ የሚችለው በማሻሻያ ምዝገባው ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ሆኖ የተጠቀሰው ሰው ብቻ ነው፡፡
3/ በተመዘገበ የመጀመሪያ ወይም የማሻሻያ ማስታወቂያ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ተብሎ የተጠቀሰው ሰው ሳይፈቅድ የተመዘገበ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም፡፡
35. በማሻሻያ ወይም በስረዛ ማስታወቂያ ላይ መካተት ያለበት መረጃ
1/ አንድ የማሻሻያ ማስታወቂያ ለዚሁ ተብሎ በተለየ ቦታ ላይ፣
ሀ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 31(1) መሠረት በመያዣ መዝገቡ የተሰጠን ልዩ የምዝገባ ቁጥር፣ እና
ለ) የሚጨመረውን ወይም የሚለወጠውን መረጃ፣
መያዝ አለበት፡፡
2/ የማሻሻያ ማስታወቂያው በተመዘገበ ማስታወቂያ ውስጥ ያለ መረጃ አንዱን ወይም ከአንድ በላይ የሆነውን ሊመለከት ይችላል፡፡
3/ አንድ የስረዛ ማስታወቂያ ለመጀመሪያ ማስታወቂያው የተሰጠውን ልዩ የምዝገባ ቁጥር ለዚሁ በተለየ ቦታ ላይ ማሳየት ይኖርበታል፡፡
36. አስገዳጅ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ ምዝገባ
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
ሀ) የማሻሻያ ማስታወቂያው መያዣ ሰጪው ከፈቀደው በላይ በላይ መረጃ የያዘ እንደሆነ፣ ወይም
ለ) የተመዘገበው ማስታወቂያ የተወሰነ የዋስትና መያዣን የሚያሰርዝ ሆኖ ከተሻሻለ፣
የማሻሻያ ማስታወቂያ ማስመዝገብ አለበት፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
ሀ) መያዣ ሰጪው የመጀመሪያ ማስታወቂያ እንዲመዘገብ ካልፈቀደ፣
ለ) መያዣ ሰጪው የመጀመሪያው ምዝገባ እንዲፈጸም ፈቃዱን ከሰጠ በኋላ የሰጠውን ፈቃድ ካነሳ እና የዋስትና ስምምነት ካልተፈረመ፣ ወይም
ሐ) ማስታወቂያው የሚመለከተው የዋስትና መብት ቀሪ እንደሆነ እና ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ለመያዣ ሰጪው ክፍያ የመፈፀም ተጨማሪ ግዴታ ከሌለበት፣
የስረዛ ማስታወቂያ መመዝገብ አለበት፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና 2(ሀ) የተገለጸው ሁኔታ ሲኖር ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ግዴታውን ለመወጣት ክፍያ መጠየቅ ወይም መቀበል አይችልም፡፡
4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) ከተደነገጉት ሁኔታዎች አንዱ ከተሟላ መያዣ ሰጪው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ እንዲያስመዘግብ በጽሑፍ መጠየቅ የሚችል ሲሆን፣ ገንዘብ ጠያቂው ይህንን ለማድረግ ምንም ዓይነት ክፍያ ወይም ወጪ መጠየቅ ወይም መቀበል አይችልም፡፡
5/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከመያዣ ሰጪው በጽሁፍ በደረሰው ጥያቄ መሠረት በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ካልፈፀመ መያዣ ሰጪው የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያው በመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲመዘገብ መጠየቅ ይችላል፡፡
6/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት የሚጠየቅን የማሻሻያ ወይም የስረዛ ማስታወቂያ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ወዲያውኑ መዝግቦ ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ ግልባጭ የሚደረግ ተገቢ ትዕዛዝ መስጠት አለበት፡፡
37. የመፈለጊያ መስፈረት
ለሕዝብ ክፍት በሆነው የመያዣ መዝገብ ውስጥ ያለን መረጃ፣
1/ የመያዣ ሰጪውን መለያ፣ ወይም
2/ የመያዣን መለያ ቁጥር፣
በመጠቀም መፈለግ ይችላል፡፡
38. ስለፍለጋ ውጤት
1/ በዚህ ክፍል የተገለጹትን መስፈርቶች ያሟላ የፍለጋ ጥያቄ ሲቀርብ የመያዣ ምዝገባ ሥርዓቱ ወዲያውኑ፣
ሀ) ፍለጋው የተከናወነበትን ቀን እና ሰዓት፣
ለ) እያንዳንዱ ከፍለጋው መሥፈርት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል መረጃ፣ ወይም
ሐ) ከፍለጋው መሥፈርት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል መረጃ አለመገኘቱን፣
የሚያሳይ ምላሽ ይሰጣል፡፡
2/ ተቃራኒ ማስረጃ እስከሌለ ድረስ በመያዣ መዝገቡ ለፍለጋ ጥያቄ የተሰጠ ማስረጃ ስለ ፍለጋው ይዘት ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
39. ማስታወቂያ ውስጥ የገባ የአስፈላጊ መረጃ ስህተት
1/ የመያዣ ሰጪው መለያ ላይ የተፈጠረ ስህተት የማስታወቂያ ምዝገባው ተፈፃሚ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡
2/ በአንድ የመያዣ ሰጪ መለያ ላይ የተፈጠረ ስህተት በሌሎች በትክክል የተገለጹ መያዣ ሰጪዎች ላይ ምዝገባው ተፈፃሚ እንዳይሆን አያደርግም፡፡
3/ ከመያዣ ሰጪው መለያ በስተቀር በሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ላይ የተፈጠረ ስህተት አንድ ምክንያታዊ የሆነ መረጃ ፈላጊን በከባዱ የሚያሳስት እስካልሆነ ድረስ ምዝገባው ተፈፃሚ እንዳይሆን አያደርግም፡፡
4/ ለስታቲስቲክስ ተብሎ በመመሪያ እንዲመዘገቡ በተጠየቁ መረጃዎች ላይ የተፈጠረ ስህተት የምዝገባውን ተፈፃሚነት አያስቀርም፡፡
5/ በአንድ የዋስትና መግለጫ ላይ የተፈጠረ ስህተት ሌላ በበቂ ሁኔታ የተገለፀ መያዥ ማስታወቂያ ምዝገባን ተፈፃሚነት አያስቀርም፡፡
6/ የመለያ ቁጥር ያለው ዋስትናን መለያ ቁጥር መሳሳት ምዝገባውን በንብረቱ ገዢ እና ተከራይ ረገድ ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡

40. ከምዝገባ በኋላ የመያዣ ሰጪው መለያ መለወጥ
1/ መያዣ ሰጪው መለያውን ከመቀየሩ ቢያንስ ከአሥር ቀናት በፊት ስለለውጡ ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
2/ ከምዝገባ በኋላ የመያዣ ሰጪው መለያ ከተለወጠ፡ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ስለለውጡ ማስታወቂያ ከደረሰው በኋላ ባሉት አሥር ቀናት ውስጥ እና የተመዘገበው ማስታወቂያ የተፈፃሚነት ጊዜ ከማብቃቱ በፊት የማሻሻያ ማስታወቂያውን ካስመዘገበ፣ ማስታወቂያው የሚመለከተው የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ያለው ተፈፃሚነት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን ከለውጡ በፊት ከተወዳዳሪ መብት ጠያቂዎች የነበረው ቀደምትነትም የተጠበቀ ይሆናል፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተው ጊዜ ካበቃ በኋላ የማሻሻያ ማስታወቂያ ካስመዘገበ፣
ሀ) ማስታወቂያ የተመዘገበበት ወይም የመያዣ ሰጪው መለያ ከተለወጠ በኋላ ነገር ግን ማሻሻያው ከመመዝገቡ በፊት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የዋስትና መብት፣ የማሻሻያ ማስታወቂያው ከሚመለከተው የዋስትና መብት ቀደምትነት ይኖረዋል፣ እና
ለ) ከመያዣ ሰጪው መለያ ለዉጥ በኋላ ነገር ግን ከማሻሻያ ማስታወቂያው ምዝገባ በፊት መያዣውን የገዛ፣ የተከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብቱን የማሻሻያ ማስታወቂያው ከሚመለከተው የዋስትና መብት ነፃ ሆኖ ያገኛል፡፡
41. ከምዝገባ በኋላ ስለሚተላለፍ መያዣ
የተመዘገበና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የዋስትና መያዣ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መያዣው ለሌላ ሰው ከተሰጠ ወይም ከተላለፈ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ያለው የተፈፃሚነት መብት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን፣ ከተፎካካሪ መብት ጠያቂዎች ያለው ቀደምትነትም የተጠበቀ ነው፡፡
42. በመያዣ መዝገብ ውስጥ ስለተመዘገበው መረጃ ተአማኒነት
1/ የዚህ አዋጅ አንቀጽ 36(6) እንደተጠበቀ ሆኖ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ማንኛውም የተመዘገበ ማስታወቂያ ውስጥ ያለን መረጃ ማሻሻል ወይም መሰረዝ አይችልም፡፡
2/ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በመዝገቡ ውስጥ የሚገኝ መረጃን ጠብቆ የማቆየት እና መረጃው ሲጠፋ ወይም ሲጐዳ መልሶ የማደራጀት ግዴታ አለበት፡፡
43. መረጃን ከመያዣ መዝገብ እና ከማህደር ስለማስወገድ
1/ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ለሕዝብ ክፍት በሆነው የምዝገባ ማስታወቂያ ውስጥ ያለን መረጃ የማስታወቂያው ምዝገባ የተፈፃሚነት ጊዜ ሲያበቃ ማውጣት አለበት፡፡
2/ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ለሕዝብ ክፍት ከሆነው መዝገብ የተወገደ መረጃን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 37 መሠረት መልሶ ሊገኝ በሚያስችል መልኩ ለአሥር ዓመት ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
44. የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተጠያቂነት ወሰን
የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በሌሎች ሕጎች ተጠያቂነት የሚኖረው፣
1/ ለመረጃ ፈላጊው የተሰጠ ምላሽ ወይም ለመዝጋቢው የተሰጠ የተመዘገበ ማስታወቂያ ግልባጭ ውስጥ ስህተት በመፈፀም ወይም መረጃ ባለማካተት፣
2/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 36 (5) እና (6) መሠረት በዋስትና መዝገብ ውስጥ መረጃ ሲመዘገብ ስህተት በመፈፀም ወይም መረጃ ባለማስገባት ወይም ከመዝገቡ ውስጥ በስህተት መረጃ በማውጣት፣
3/ የመያዣ መዝገቡ ለመዝጋቢው የተመዘገበ ማስታወቂያ ግልባጭ ባለመስጠቱ፣ ወይም
4/ ለመዝጋቢው ወይም ለመረጃ ፈላጊው ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ በመስጠት፣
ለደረሰ ኪሣራ ወይም ጉዳት ነው፡፡

ክፍል አምስት

የቀዳሚነስትና ያለው

45. ገንዘብ ጠያቂ የቀዳሚነት መብት
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች ይልቅ የቀዳሚነት መብት አለው፡፡
2/ የኪሣራ ሕግ በተቃራኒው ካልተደነገገ በስተቀር የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ተፈጻሚነት በኪሣራ ወይም በሂሳብ ማጣራት ጊዜም ይቀጥላል፡፡
46. በአንድ የመያዣ ሰጪ ስለተፈጠሩ ተወዳዳሪ የዋስትና መብቶች
1/ የዚህ ክፍል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው አንድ መያዣ ሰጪ በተመሳሳይ ዋስትና ላይ በፈጠራቸው የዋስትና መብቶች መካከል ያለው የቀዳሚነት መብት የሚወሰነው ዋስትና የተመሰረተበት ጊዜ ቅደም ተከተል ከግምት ሳይገባ በምዝገባቸው ቅደም ተከተል ነው፡፡
2/ የዋስትና ውል ከመፈፀሙ ወይም በታሳቢ ሀብት ላይ መያዣ ሰጪው የማስያዝ መብት ወይም ስልጣን ከማግኘቱ በፊት የተመዘገበ የዋስትና መብት ቀዳሚነት የሚወሰነው በምዝገባው ቅደም ተከተል መሠረት ነው፡፡
47. በተለያዩ መያዣ ሰጪዎች ስለተፈጠሩ ተወዳዳሪ የዋስትና መብቶች
አንድ መያዣ ጪ መያዣውን ያገኘው በዚሁ መያዣ ላይ ቀደም ብሎ በሌላ ሰው የተመሰረተ የዋስትና መብት እንደተጠበቀና በሦስተኛ ወገኖች ላይም ተፈጻሚ ከሆነ፣ በመያዣው ላይ የተመሰረተው መብት ቀደም ብሎ በሌላው ሰው ከተመሰረተው የዋስትና መብት የበታች ነው፡፡
48. የዋስትና መብት መኖሩን ማወቅ ውጤት የሌለው ስለመሆኑ
ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የዋስትና መብት መኖሩን ማወቁ በዚህ አዋጅ መሠረት ያለውን የቀዳሚነት መብት አያሳጣውም፡፡
49. በሶስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ የሆነ የዋሰትና መንገድ በሚለወጥበት ጊዜ ስለሚኖሩ ተወዳዳሪ የዋስትና መብቶች
በዚህ ክፍል ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በስተቀር በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ የነበረ የዋስትና መብት የተመሠረተበት መንገድ ሲለወጥ የጊዜ ክፍተት እስከሌለው ድረስ የቀዳሚነት መብቱ የተጠበቀ ይሆናል፡፡
50. ታሳቢ ድር እና ታሳቢ መያዣ
1/ የዚህ አዋጅ አንቀጽ 55 እንደተጠበቀ ሆኖ ቀዳሚ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ በኋላ የተገቡ ግዴታዎችን ጨምሮ ሁሉንም ዋስትናቸው የተጠበቁ ግዴታዎችን ይሸፍናል፡፡
2/ ከምዝገባው በፊት ወይም በኋላ በመያዣ ሰጪው የተገኘ ወይም የተፈጠረ ቢሆኑም ቀዳሚ የዋስትና መብት በመያዣ መዝገቡ በማስታወቂያ ተለይተው የተመዘገቡ ዋስትናዎችን በሙሉ ይሸፍናል፡፡
51. በተያያዥ ገቢ ላይ ስለሚኖር ቀዳሚ የዋስትና መብት
የዚህ አዋጅ አንቀጽ 58 እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 14 መሠረት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ የሆነ የተያያዥ ገቢ ዋስትና መብት ከተወዳዳሪ የዋስትና መብት ይልቅ የገቢው ምንጭ በሆነው ዋስትና ላይ በተመሠረተው የቀዳሚነት መብት መሠረት ተፊፃሚ ይሆናል፡፡
52. ውህድ ወይም ምርት ውስጥ የተቀላቀሉ ግዑዝ ሀብቶች ላይ ሰለሚኖር ቀዳሚ የዋስትና መብት
1/ የተቀላቀሉ ወይም የተዋሃዱ ዕቃዎች ከአንድ ለሚበልጥ የዋስትና መብት ከዋሉ ዕቃዎቹ ከመቀላቀላቸው በፊት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነው የዋስትና መብት ዕቃዎቹ ከተቀላቀሉ በኋላ ከሚመሰረት የዋስትና መብት በፊት የቀዳሚነት መብት አለው፡፡
2/ የተቀላቀሉ ወይም የተዋሃዱ ዕቃዎች ከአንድ ለሚበልጥ የዋስትና መብቶች ከዋሉና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆኑ የመብቶቹ ቀዳሚነትና ዋጋ ዕቃዎቹ በተዋሃዱበት ጊዜ ባለው መሠረት ይሆናል፡፡
53. በማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ ላይ ስለሚኖር ቀዳሚ የዋስትና መብት
1/ የዋስትና መብት የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ በሆኑ ወይም ሊሆኑ በሚችሉ ግዑዝ ሀብቶች ላይ ሊመሠረት ወይም ሊቀጥል ይችላል፡፡ ሆኖም መብቱ በመደበኛ የግንባታ ዕቃዎች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡
2/ በዚህ አዋጅ መሠረት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ የዋስትና መብት በሌሎች ህጎች ከተመሠረቱና ተፈፃሚ ከሆኑ ተወዳዳሪ መብቶች ይልቅ የቀዳሚነት መብት አለው፡፡
54. መያዣውን የገዛ፣ የተላለፈለት፣ የተከራየ ወይም እንዲጠቀም ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብቶች
1/ የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ሆኖ እያለ መያዣው በሽያጭ ወይም በሌላ ሁኔታ ከተላለፈ፣ ከተከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ከተሰጠ ገዢው ወይም መብቱ የተላለፈለት፣ የተከራየ ወይም የተፈቀደለት በዚህ አንቀጽ እንደተደነገገው ካልሆነ በስተቀር የንብረቱ ባለመብት የሚሆነው በላዩ ላይ ያለው የዋስትና መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ንብረቱን ከዋስትና ነፃ ሆኖ እንዲተላለፍ የፈቀደ እንደሆነ መያዣው በግዢ ወይም በሌላ ሁኔታ የተላለፈለት ሰው መብቱን ከዋስትናው ነፃ በሆነ ሁኔታ ያገኛል፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ከዋስትናው ነፃ በሆነ ሁኔታ እንዲያከራይ ወይም የመጠቀም ፈቃድ እንዲሰጥ ለመያዣ ሰጪው የፈቀደ እንደሆነ ተከራዩ ወይም የመጠቀም ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብት በዋስትናው መብት አይታወክም፡፡
4/ በሻጩ መደበኛ የንግድ ሥራ ውስጥ ገዢው የሽያጭ ውሉን በተዋዋለበት ወቅት ንብረቱ ለመያዣ መዋሉንና ሻጩ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን መብት የጣሰ መሆኑን ካላወቀ በግዥው የሚያገኛቸው መብቶች ከዋስትናው ነፃ ናቸው፡፡
5/ በአከራዩ መደበኛ የንግድ ሥራ ውስጥ ተከራዩ የኪራይ ውሉን በተዋዋለበት ወቅት ንብረቱ ለመያዣ መዋሉንና ኪራዩ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን መብት የጣሰ መሆኑን ካላወቀ በኪራዩ የሚያገኛቸው መብቶች ከዋስትናው ነፃ ናቸው፡፡
6/ በፈቃድ ሰጪው መደበኛ የንግድ ሥራ ውስጥ ፈቃድ ተቀባዩ አዕምሯዊ ንብረትን ለመጠቀም የፈቃድ ውሉን በተዋዋለበት ወቅት አዕምሯዊ ንብረቱ ለዋስትና መዋሉንና ፈቃዱ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን መብት የሚጥስ መሆኑን ካላወቀ በፈቃዱ የሚያገኛቸው መብቶች ከዋስትናው ነፃ ናቸው፡፡
7/ አንድን መያዣ የገዛ ወይም በሌላ መንገድ የተላለፈለት ሰው መብቶቹን ከዋስትናው ነፃ በሆነ ሁኔታ ካገኛቸው ቀጣዩ ገዢ ወይም መብቱ የሚተላለፍለት ስው መብቶቹን የሚያገኘው ከዋስትናው ነፃ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡
8/ አንድ በዋስትና የተያዘ ግዑዝነት ያለው ወይም የሌለውን ሀብት ከዋስትና ነፃ የተከራየ ወይም ፈቃድ የተቀበለ ከሆነ የቀጣዩ ተከራይም ሆነ ፈቃድ ተቀባይ መብቶች በዋስትናው አይታወኩም፡፡
55. በህግ ወይም በፍርድ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው መብቶች
1/ በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው የዋስትና መብቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከመሆኑ አስቀድሞ በመያዣ መዝገብ ውስጥ ይህንኑ ካስመዘገበ መብቱ ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
2/ በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው ማስታወቂያ ከመመዝገቡ አስቀድሞ የዋስትና መብቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነ ይኼው መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የቀዳሚነት መብት፣
ሀ) በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው በመያዣ መዝገቡ ውስጥ ስለመመዝገቡ ማስታወቂያ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በሰላሳ የሥራ ቀናት ውስጥ፣ ወይም
ለ) መጠኑ አስቀድሞ የተወሰነ ወይም ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ተለይቶ በተቀመጠ ቀመር መሠረት በተወሰነ ገንዘብ ወይም የማይሻር ግዴታ በተገባለትና በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው ለመያዣ ሰጪው ማስታወቂያ ከመስጠቱ በፊት፣
በተሰጠ ብድር ላይ ብቻ የተወሰነ ይሆናል፡፡
3/ በመደበኛ የንግድ ሥራ ሂደት ለሚቀርቡ የአገልግሎት ወይም የአቅርቦት ክፍያን ወይም አፈጻጸምን ለማረጋገጥ ዕቃዎችን ለዋስትና በይዞታ ሥር ለማቆየት የሚያስችል የዋስትና መብት እስካለ ድረስ ይህ የይዞታ መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
56. ከተገኘ የዋስትና መብት ጋር የሚወዳደር ሌላ የዋስትና መብት
1/ በፍጆታ ዕቃዎች፣ በመሣሪያዎች እና በአዕምሯዊ ንብረቶች ላይ የተገኘ የዋስትና መብት መያዣ ሰጪው ከመሠረተው ሌላ ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ቀዳሚነት የሚኖረው፣
ሀ) የተገኘ የዋስትና መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ንብረቱን በይዞታው ሥር ካደረገ፣ ወይም
ለ) መያዣ ሰጪው ሀብቱን በይዞታው ሥር ባደረገ ወይም አዕምሯዊው ንብረት ላይ መብት ባገኘ በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ የተገኘ የዋስትና መብት ማስታወቂያ የተመዘገበ እንደሆነ፣
ነው፡፡
2/ በንግድ ዕቃ ላይ የተገኘ የዋስትና መብት መያዣ ሰጪው ከመሠረተው ሌላ ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ቀዳሚነት የሚኖረው፣
ሀ) የተገኘ የዋስትና መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን በይዞታው ሥር ካደረገ፣ ወይም
ለ) መያዣ ሰጪው ሀብቱን በይዞታው ሥር ከማድረጉ ቀደም ብሎ የተገኘ የዋስትና መብት ማስታወቂያ የተመዘገበ ከሆነ፣ እና
ሐ/ የተገኘ የዋስትና መብት ያለው ሰው በተመሳሳይ አይነት መያዣ ላይ ማስታወቂያ ለመዘገበና ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ በመያዣው የዋስትና መብት እንዳለው ወይም ለማግኘት ማቀዱን ካስታወቀው፣
ነው፡፡
57. የተገኙ የዋስትና መብቶች ተወዳዳሪነት
1/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተወዳዳሪ በሆኑ የተገኙ የዋስትና መብቶች መካከል ቀዳሚነት የሚወሰነው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 46 መሠረት ነው፡፡
2/ የሻጭ፣ የአከራይ ወይም የፈቃድ ሰጪ የተገኘ የዋስትና መብት ዋስትና ካለው ተወዳዳሪ ገንዘብ ጠያቂ መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
58. በተያያዥ ገቢ ላይ የተገኘ የዋስትና መብት
1/ በመሣሪያ ላይ የተገኘ የዋስትና መብት ካለ በሀብቱ ተያያዥ ገቢ ላይ የሚኖር የቀዳሚነት መብት ከተገኘ የዋስትና መብት ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡፡
2/ በአዕምሯዊ ንብረት ወይም በንግድ ዕቃ ላይ የተገኘ ቀዳሚ የዋስትና መብት ካለ በንብረቱ ተያያዥ ገቢ ላይም የቀዳሚነት መብቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ሆኖም ገቢው ተሰብሳቢ ሂሳብ፣ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ፤ የንግድ ወረቀት ወይም ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ከሚገባ ገንዘብ ላይ ክፍያ የመጠየቅ መብት ከሆነ ቀዳሚነቱ አይሠራም፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ የተመለከተው የቀዳሚነት መብት የሚፀናው የተገኘ የዋስትና መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ተያያዥ ገቢው ከመገኘቱ በፊት በመያዣ መዝገብ ውስጥ ማስታወቂያ ስለመመዝገቡ በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂነት መብት ለተሰጣቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ያስታወቃቸው እንደሆነ ነው፡፡
59. ከውህድ ወይም ምርት ጋር የተቀላቀሉ ግዑዝ ሀብቶች ላይ የተገኝ የዋስትና መብት
ውህድ ወይም ምርትን በሚሸፍንና ግዑዝ ሀብት ላይ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የተገኝ የዋስትና መብት በተመሳሳይ መያዣ ሰጪ ከተመሠረተ ሌላ የዋስትና መብት ይልቅ ቀዳሚነት አለው፡፡
60. የቀዳሚነት መብትን ስለማሳለፍ
1/ ማንኛውም ሰው በማናቸውም ጊዜ በዚህ አዋጅ የተሰጠውን የቀዳሚነት መብት ለማንኛውም ነባራዊ ወይም ታሳቢ ተወዳዳሪ የዋስትና ባለመብት ተጠቃሚውን ወገን ተዋዋይ ማድረግ ሳያስፈልግ የቅድሚያ መብቱን አሳልፎ መስጠት ይችላል፡፡
2/ የቀዳሚነት መብትን ማሳለፍ መብቱን ካሳለፈው ሰው እና ከተጠቃሚው ውጪ የሌሎች ተወዳዳሪ ባለመብቶችን አያውክም፡፡
61. የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች
1/ በዋስትና ከተመዘገበና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚነት ካለው የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ የዋስትና መብት ይልቅ ሰነዱን በይዞታው ሥር ለዋስትና ያደረገ ባለመብት ቀዳሚነት አለው፡፡
2/ በዋስትና የተያዘና መብቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድን ገዥው ወይም በህግ የተላለፈለት ሰው ከዋስትናው ነፃ በሆነ መንገድ ሊያገኝ የሚችለው፣
ሀ) ሰነዶቹን በንግድ ሕጉ መሠረት እንደያዘ የሚቆጠር ከሆነ፣ ወይም
ለ) ሰነዶቹን በይዞታው ሥር ካደረገ እና ሽያጩ ወይም ዝውውሩ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብት እንደሚጥስ ባለማወቅ ዋጋ ከከፈለ፣
ነው፡፡
62. በተቀማጭ ሂሳብ ውስጥ ከሚገባ ገንዘብ ክፍያን የመጠየቅ መብት
1/ ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ከሚገባ ገንዘብ ላይ ክፍያ የመጠየቅ የዋስትና መብት ያለውና ሂሳቡ በይዞታው ስር የሚገኝ ባለመብት በሌላ ማንኛውም መንገድ ከሚገኝና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሚሆን የዋስትና መብት ይልቅ ቀዳሚነት አለው፡፡
2/ ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ውስጥ ከሚገባ ገንዘብ ክፍያ የመጠየቅ የዋስትና መብት ያለው የፋይናንስ ተቋም ከሆነ፣ የዋስትና መብት ያለው ሌላ ክፍያ ጠያቂ የሂሳቡ ባለይዞታ በመሆን በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ካደረገው ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ውጪ በሌላ ማንኛውም መንገድ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነው ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ይልቅ ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
3/ በቁጥጥር ስምምነት አማካኝነት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ በሆነና ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ከሚገባ ገንዘብ ክፍያ የመጠየቅ መብት ላይ ያለ የዋስትና መብት፣
ሀ) ከፋይናንስ ተቋሙ የዋስትና መብት፣ ወይም
ለ) የሂሳቡ ባለይዞታ የሆነ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ካደረገው የዋስትና መብት፣
በስተቀር ከሌላ ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
4/ ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ከሚገባ ገንዘብ ክፍያ የመጠየቅ መብት ያላቸውና በቁጥጥር ስምምነት አማካይነት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆኑ ተወዳዳሪ የዋስትና መብቶች መካከል ቀዳሚነት የሚወሰነው የቁጥጥር ስምምነት የተደረጉበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
5/ ወደ ተቀማጭ ሂሳብ ከሚገባ ገንዘብ ክፍያ የመጠየቅ የዋስትና መብት ካለው ሰው ይልቅ አንድ የፋይናንስ ተቋም የተበዳሪውን ዕዳ ለማቻቻል ያለው መብት ቀዳሚነት አለው፤ ሆኖም ይህ የቀዳሚነት መብት የሂሳቡ ባለይዞታ በመሆን የዋስትና መብቱን በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ያደረገ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን የዋስትና መብት አይጥስም፡፡
6/ በመያዣ ሰጪው ፈቃድ ወይም አማካኝነት ከአንድ ተቀማጭ ሂሳብ ላይ ገንዘብ የተላለፈለት ሰው ይህ ዝውውር ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብትን የሚጥስ መሆኑን ካላወቀ ገንዘቡን ከዋስትና ነፃ በሆነ መንገድ ያገኛል፡፡
63. ገንዘብ
በዋስትና መብት ከተያዘ ገንዘብ ላይ ዝውውር የተፈፀመለት ሰው ገንዘቡን ከዋስትና ነፃ በሆነ መንገድ ሊያገኝ የሚችለው ዝውውሩ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብትን የሚጥስ መሆኑን ካላወቀ ብቻ ነው፡፡
64. ተላላፊ ሰነድ እና በሰነዱ የሚሸፈኑ ግዑዝ ሀብቶች
1/ የሚተላላፍ ሰነድን በይዞታ ሥር በማድረግ ሰነዱ በሚሸፍነው ንብረት ላይ ተፈፃሚ የሆነ የዋስትና መብት በሌላ ማንኛውም መንገድ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነው ተወዳዳሪ የዋስትና መብቱ ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
2/ በዋስትና የተያዘ ተላላፊ ሰነድ የተላለፈለት ሰው ሰነዱን ተቀብሎ በይዞታው ሥር ካደረገ፣ የንብረት ሽያጩ ወይም ዝውውሩ ሌላ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብትን እንደሚጎዳ ባለማወቅ ዋጋ ከፍሎበት ከሆነ፤ መብቱ በሰነዱ ወይም በሰነዱ በተሸፈኑ ግዑዝ ሀብቶች ላይ ካለ እና በዚህ አዋጅ መሠረት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነው የዋስትና መብት ነፃ ሆኖ ያገኛል፡፡
65. ሴኩሪቲዎች
1/ በሰነድ የተደገፋ ሴኩሪቲዎችን በይዞታው ሥር በማድረግ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ያደረገ የዋስትና መያዣ መብት፣ መያዣ ሰጪው በሴኩሪቲዎች ላይ ከፈጠረውና ማስታወቂያ ለማስመዝገብ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ካደረገው ሌላ ተፎካካሪ የዋስትና መብት ቀደምትነት ይኖረዋል፡፡
2/ በአውጪው ወይም እርሱን በመወከል በኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ላይ ስለዋስትና መያዣ መብት በተዘጋጀ መዝገብ ላይ መግለጫ በመጻፍ ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን ስም እንደባለመብት መመዝገብ በሴኩሪቲዎቹ ላይ በሌላ ማንኛውም መንገድ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነው የዋስትና መብት ይልቅ በምዝገባው የተገኘው መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
3/ የቁጥጥር ስምምነት በመፈራረም በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆነ የኤሌክትሮኒክ
ሴኩሪቲዎች የዋስትና መብት በእነዚሁ ሴኩሪቲዎች ላይ ማስታወቂያ በማስመዝገብ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ ከሆነው የዋስትና መብት ይልቅ ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
4/ በቁጥጥር ስምምነቶች አማካኝነት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚ የሆኑ ተወዳዳሪ የኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ላይ የዋስትና መብቶች መካከል ቀዳሚነት የሚወሰነው ስምምነቶቹ የተደረጉበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
5/ በሰነድ የተደገፉ ሴኩሪቲዎችን በይዞታው ሥር ያደረገ ወይም የኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ላይ መብት ያገኘና መብቱ የተላለፈለት ሰው ሽያጩ ወይም ዝውውሩ በዋስትና ውሉ መሠረት ዋስትና ያለው ሌላ ገንዘብ ጠያቂን መብት እንደሚጥስ ባለማወቅ ዋጋ ከፍሎበት ከሆነ መብቱን ከዋስትናው ነፃ ሆኖ ያገኛል፡፡
ክፍል ስድስት
የተዋዋይ ወገኖች እና ሦስተኛ ወገን ተገዳጆች መብትና ግዴታ
66. መያዣውን በይዞታው ሥር ካደረገ ሰው የሚጠበቅ ግዴታ
አንድ የመያዣ ሰጪ ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በይዞታው ሥር የሚገኝ መያዣን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ መጠበቅ አለበት፡፡
67. ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ግዴታ
የዋስትና መብት በሚቋረጥበት ጊዜ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
1/ በይዞታው ሥር ያለውን ዋስትና ለመያዣ ሰጪው ይመልስለታል፣
2/ ያስመዘገበውን የዋስትና ማስታወቂያ በአንቀጽ 36(2) (ሐ) መሠረት ይሰርዛል፣
3/ በቁጥጥር ስምምነት መሠረት ስምምነቱን ያነሳል፡፡
68. መያዣውን የመጠቀም፣ ወጪው እንዲተካ የማድረግ እና የመቆጣጠር መብት
1/ ዋስትናው በይዞታው ሥር የሆነ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
ሀ) የመድን፣ የግብር እና ሌሎች ክፍያዎችን ጨምሮ ሀብቱን ለመጠበቅ ያወጣው ተገቢ የሆነ ወጪ እንዲተካለትና ወጪውም ዋስትናው በተጠበቀው ግዴታ ላይ እንዲታከል የማድረግ መብት አለው፣
ለ) መያዣውን በአግባቡ በመጠቀም፣ ከመያዣውም ይገኛል ተብሎ ስምምነት የተደረገበትን ገቢ ዋስትና ለተገባለት ግዴታ ክፍያ ማዋል ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በመያዣ ሰጪው ወይም በሌላ ሰው ይዞታ ሥር ያለን መያዣ የመቆጣጠር መብት አለው፡፡
69. መረጃ የማግኘት መብት
1/ መያዣ ሰጪው ዋስትና የተገባለትን ግዴታ ወይም መያዣውን በሚመለከት መረጃ እንዲሰጠው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን መጠየቅ ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መረጃ እንዲሰጥ ጥያቄ በቀረበለት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለመያዣ ሰጪው ወይም መያዣ ሰጪው ለወከለው ሰው፣
ሀ) ዋስትና ተገብቶለት ነገር ግን ስላልተከፈለ ግዴታ የሂሳብ መግለጫ፣
ለ) ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በየትኛው ዋስትና ላይ የዋስትና መብት እንዳለው የሚያመለክት መግለጫ፣ ወይም
ሐ) ዋስትና ተገብቶለት ነገር ግን ስላልተከፈለ ግዴታ ሂሳብ የሚገልጽና የዋስትና መያዣ መብቱ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ዋስትና የሚያመለክት መግለጫ፣
መስጠት አለበት፡፡
70. የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ ስለሚደረግለት ጥበቃ
በዚህ አዋጅ በተቃራኒው ካልተደነገገ በስተቀር በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የዋስትና መብት መመሥረት ለሂሳቡ መነሻ በሆነው ዋናው ውል የተካተቱ የክፍያ ሁኔታዎችን ጨምሮ የባለዕዳውን መብትና ግዴታ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ አያውክም፡፡
71. በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የዋስትና መብትንና ክፍያን ስለማሳወቅ
1/ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የዋስትና መብት ተፈፃሚነት የሚኖረው ባለዕዳው በዋስትና የተያዘውን ተሰብሳቢ ሂሳብና ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን በሚገባ የለየ ማስታወቂያ ሲደርሰው ነው፡፡
2/ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የተመሠረተ የዋስትና መብት ከማስታወቂያ በኋላ የሚፈጠር ተሰብሳቢ ሂሳብንም ሊያካትት ይችላል፡፡
3/ የተሰበሳቢ ሂሳቡ ባለዕዳ ስለተመሰረተው የዋስትና መብት ማስታወቂያ እስከሚደርሰው ድረስ በዋናው ውል መሠረት የክፍያ ግዴታውን ይፈፅማል፡፡ ባለዕዳው ማስታወቂያው ከደረሰው በኋላ ከግዴታው ነፃ የሚሆነው ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ ክፍያን በመፈፀም ወይም በማስታወቂያው ወይም በገንዘብ ጠያቂው በጽሑፍ ተቃራኒ ማሳወቂያ ከተሰጠው ብቻ ነው፡፡
4/ የተሰብሳቢ ሂሳቡ ባለዕዳ በተሰብሳቢ ሂሳቡ ላይ ስለተመሰረተና ከአንድ በላይ የሆነ የዋስትና መብት ማስታወቂያ ከመያዣ ሰጪው ከደረሰው መጀመሪያ በደረሰው ማስታወቂያ መሠረት ክፍያ በመፈፀም ከግዴታው ነፃ ይሆናል፡፡
5/ የተሰብሳቢ ሂሳቡ ባለዕዳ ዋስትና ያለውን ገንዘብ ጠያቂ በተሰብሳቢው ሂሳብ ላይ የዋስትና መብት ለመኖሩ ተገቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ በቂ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሊጠይቀው ይችላል፡፡ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ መሠረት እስከሚፈፅም ድረስ የተሰብሳቢ ሂሳቡ ባለዕዳ ስለዋስትና መብቱ ማስታወቂያ ቢደርሰውም እንኳን ለመያዣ ሰጪው ክፍያ በመፈፀም ግዴታውን መወጣት ይችላል፡፡
72. የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ መቃወሚያዎችና የማቻቻል መብት
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳን በዋስትና የተያዘውን ተሰብሳቢ ሂሳብ እንዲከፍል ጥያቄ ሲያቀርብ የተሰብሳቢ ሂሳቡ ባለዕዳ በገንዘብ ጠያቂው ላይ በመቃወሚያነት፣
ሀ) ለተሰብሳቢ ሂሳቡ መመስረት ምክንያት ከሆነው ውል የሚመነጩ መቃወሚያዎችንና የማቻቻል መብትን ወይም የዚሁ አካል ሌላ ግብይትን በመጥቀስ የዋስትና መብቱ እንዳልተመሰረተ፣
ለ) ባለዕዳው ስለዋስትና መብቱ ማስታወቂያ በደረሰው ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችለውን የማቻቻያ መብት፣
ማንሳት ይችላል፡፡
2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም፣ የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ የዚህ አዋጅ አንቀጽ 9 ስምምነት ተጥሷል የሚል የመከላከያ ወይም መብት የማቻቻል ጥያቄ በማንሳት መያዣ ሰጪው በተሰብሳቢ ሂሳቡ ላይ ያለውን ዋስትና የመመስረት መብት በማንኛውም ሁኔታ ሊገድብበት አይችልም፡፡
3/ የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከቱ መቃወሚያዎችንና የማቻቻል መብትን ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ላይ ላለማንሳት ከመያዣ ሰጪው ጋር በጽሑፍ ለመስማማት ይችላል፡፡ ሆኖም ዋስትና ከተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ የማጭበርበር ተግባር የሚመነጩ ወይም በራሱ ችሎታ ማጣት ላይ የተመሠረቱ መቃወሚያዎችን አያስቀርም፡፡
73. ተሰብሳቢ ሂሳብ የተመሠረተበትን ዋና ውል ስለማሻሻል
በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ስለተመሠረተ የዋስትና መብት ማስታወቂያ ከመሰጠቱ በፊት በመያዣ ሰጪውና በባለዕዳው መካከል የተፈረመ የዋናው ውል ማንኛውም ማሻሻያ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብትን የሚነካ ቢሆንም ተፈፃሚ ነው፤ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂም በተሻሻለው ውል መሰረት የሚመለከተውን መብት ያገኛል፡፡
74. የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ የፈፀማቸውን ክፍያዎች ስለማስመለስ
በመያዣ ሰጪው ወይም በውል የተሰብሳቢ ሂሳብን ሙሉ በሙሉ ያስተላላፈ ሰው የተሰብሳቢው ሂሳብ መነሻ የሆነውን ውል መፈፀም ባለመቻሉ ባለዕዳው ለመያዣ ሰጪው ወይም ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ የከፈለውን ገንዘብ የማስመለስ መብት አይሰጠውም፡፡
75. ከሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ የመሰብሰብ ፈቃድ ከተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት ተጻራሪ የሆነ መብት
1/ በተቀማጭ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ከሚደረግ ገንዘብ ላይ ክፍያ የማግኘት የዋስትና መብት ሲመሰረት፣ ከሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ የመሰብሰብ ፈቃድ ያለው የፋይናንስ ተቋም ለዋስትና መብቱ መመሥረት ይሁንታውን ካልሰጠ በስተቀር መብቱና ግዴታው የተጠበቀ ሲሆን ለሦስተኛ ወገኖችም ስለሂሳቡ ማንኛውንም መረጃ እንዲሰጥ አይገደድም፡፡
2/ በፋይናንስ ተቋሙ ውስጥ ከተከፈተ የተቀማጭ ሂሳብ ላይ ተቋሙ ያለውን ማንኛውም የማቻቻል መብትና በተቀማጭ ሂሳቡ ገቢ ከሚደረግ ገንዘብ ክፍያ የማግኘት የዋስትና መብቱን አያውክም፡፡
ክፍል ሰባት
የዋስትና መብት ማስከበር
76. ከግዴታ አለመፈፀም በኋላ ስለሚኖሩ መብቶች
1/ ከግዴታ አለመፈጸም በኋላ በመያዣው ላይ ያለ መብትን መጠቀም ዋስትና የተገባለት ግዴታ የማስፈጸም መብት መጠቀምን አያስቀርም፤ ከግዴታ አለመፈጸም በኋላ ዋስትና የተገባለት ግዴታ የማስፈጸም መብትን መጠቀም በመያዣው ላይ ያለ መብት መጠቀምን አይከለክልም፡፡
2/ መያዣ ሰጪው እና ዋስትና የተገባለት ግዴታን የመክፈል ወይም የመፈጸም ሃላፊነት ያለበት ሌላ ማንኛውም ሰው በዚህ ክፍል ድንጋጌዎች ሥር ያሉትን መብቶች በራሱ መተው ወይም በስምምነት ማሻሻል አይችልም፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ ክፍል ሥር ያሉትን መብቶች በቅን ልቦና እና ተገቢ በሆነ የንግድ አሠራር መሠረት መጠቀም አለበት፡፡
77. ባልተከበረ ግዴታ ላይ ዳኝነት ስለመጠየቅ
1/ ማንኛውም የዚህ ክፍል ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው ምክንያት ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብቱ በሌላ ሰው የተነካበት ከሆነ ዳኝነት እንዲሰጠው ለፍርድ ቤት ማመልከት የሚችል ሲሆን፣ ይህም በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት መዳኘትን ይጨምራል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በአንቀፅ 82(4) ላይ የተደነገጉትን የፍትሐብሔር የጨረታ ሽያጭ አፈፃፀም ስነስርአቶች በመተላለፍ በባለዕዳው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ተጠያቂነት አለበት፡፡
78. በማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ ላይ መብትን ስለማስከበር
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ ላይ ያገኘውን የዋስትና መብት በዚህ ክፍል ድንጋጌዎች መሠረት ማስከበር ይችላል፡፡
2/ የአንድ ግዴታ አፈጻጸም በመያዣ ሰጪው ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና ከተገባለት፡ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በምርጫው፣
ሀ) በተንቀሳቃሽ ንብረት የዋስትና መብት ማስከበር ድንጋጌዎች መሠረት በተንቀሳቃሽ ንብረቱ ላይ ያለውን የዋስትና መብት፣
ለ) በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና መብት የማስከበር ድንጋጌዎች መሠረት በማይንቀሳቀስ ንብረቱ ላይ ያለውን የዋስትና መብት፣ ወይም
ሐ) በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና መብት የማስከበር ድንጋጌዎች መሠረት በሁለቱም ዓይነት ንብረቶች ላይ ያገኘውን የዋስትና መብት፣
ማስከበር ይችላል፡፡
79. መልሶ ስለመውሰድ መብት
1/ በዚህ ክፍል ድንጋጌዎች የመብት ማስከበር ሂደት መብቱ የተነካበት ማንኛውም ሰው ተገቢ የሆነ የማስከበር ወጪን ጨምሮ ዋስትና የተገባለት ግዴታን በመክፈል ወይም በመፈጸም መያዣውን መልሶ መውሰድ ይችላል፡፡
2/ መያዣ ሰጪው ያለው መያዣውን መልሶ የመውሰድ መብት ሌላ ማንኛውም ሰው መያዣውን ለመውሰድ ካለው መብት ቀዳሚነት ይኖረዋል፡፡
3/ መያዣውን መልሶ የመውሰድ መብትን መያዣው እስከሚሸጥ፣ ወይም እስከሚተላለፍ ወይም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ እስከሚወስደው ወይም ለዚሁ ዓላማ ውሉ እስከሚፈጸም ድረስ መጠቀም ይቻላል፡፡
80. ቀደሚ ደረጃ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብቱን ለማስከበር ስለሚኖረው የመሪነት መብት
1/ ሌላ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ወይም በህግ ወይም በፍርድ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው የዋስትና መብቱን ማስከበር ቢጀምርም ከነዚህ መብቶች የቀዳሚነት መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ዋስትናው ከመሸጡ፣ ከመተላለፉ ወይም በሌላኛው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከመወሰዱ ወይም ይኸው ገንዘብ ጠያቂ ለዚሁ ዓላማ ውሉን ከመፈጸሙ በፊት በማንኛውም ጊዜ የዋስትና መብት የማስከበር ሂደትን በበላይነት መምራት መጀመር ይችላል፡፡
2/ ቀዳሚ ደረጃ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብት የማስከበር ሂደትን በበላይነት የመምራት መብት አንድ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ አዋጅ በተደነገገ ማንኛውም መንገድ መብቱን ለማስከበር እንዲችል የተሰጠውን መብት ያካትታል፡፡
81. ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን በይዞታው ሥር ለማድረግ ስላለው መብት
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
ሀ) ያለፍርድ ቤት ማመልከቻ መያዣውን በይዞታው ሥር ማድረግ እንደሚችል መያዣ ሰጪው በዋስትና ስምምነቱ ከፈቀደ፣
ለ) መያዣውን በይዞታው ሥር ለማድረግ በሚሞክርበት ጊዜ መያዣ ሰጪው ወይም መያዣውን በይዞታው ሥር ያደረገ ማንኛውም ሌላ ሰው ካልተቃወመ፣
መያዣውን በይዞታው ሥር ማድረግ ይችላል፡፡
2/ መያዣ ሰጪው ወይም መያዣውን በይዞታው ሥር ያደረገ ማንኛውም ሌላ ሰው መያዣውን ዋስትና ላለው ገንዘብ ጠያቂ ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ፡ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የፖሊስ ኃይል ርክክቡን እንዲያስፈጽም የማዘዝ ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ሳይወስድ በመያዣ ሰጪው ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳለ አገልግሎት መስጠት እንዳይችል ለማድረግ ወይም ለማስተላለፍ ይችላል፡፡
82. ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ለማስተላለፍ ስላለው መብት
1/ ግዴታ አለመፈጸምን ተከትሎ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ባለበት ሁኔታ ወይም ከንግድ አሠራር አንፃር ተገቢ የሆነ ዝግጅት ወይም ማሻሻል በማድረግ ለመሸጥ፣ ለማስተላለፍ፣ ለማከራየት ወይም ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ ለመስጠት ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣው የሚሸጥበት፣ የሚተላለፍበት፣ የሚከራይበት ወይም ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ የሚሰጥበትን መንገድ፣ ሁኔታ፣ ጊዜ፣ ቦታና ሌሎች ሁኔታዎች ማመቻቸት ይችላል፡፡ ይህም መያዣውን በተናጠል፣ በከፊል ወይም በጠቅላላ የመሸጥ፣ የማስተላለፍ፣ የማከራየት ወይም ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ የመስጠት ምርጫን ይጨምራል፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የመያዣውን ባለቤትነት በሐራጅ ለገዛው ሰው ማስተላለፍ፣ ወይም በሁለተኛው ሐራጅ ገዢ ካልቀረበ በመጀመሪያው ሐራጅ በተወሰነው የመነሻ ዋጋ መያዣውን የመውሰድና ባለቤትነቱም እንዲተላለፍለት ማድረግ ይችላል፡፡
4/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ሐራጅን ከመረጠ የጨረታ ሂደቱ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ከቁጥር 394-449 በተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው መሠረት መፈጸም አለበት፡፡
5/ በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች መሰረት የሚፈፀም መያዣን ማስተላለፍ መያዣ ሰጪውን በመወከል እንደተፈፀመ ይቆጠራል፡፡
83. መያዣን ለማስተላለፍ የሚሰጥ ማስታወቂያ
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን የማስተላለፍ ፍላጎት ካለው የአሥር የሥራ ቀናት ማስታወቂያ፣
ሀ) ለመያዣ ሰጪው እና ለባለዕዳው፣
ለ) በመያዣው ላይ መብት እንዳለው በጽሑፍ ላሳወቀው ማንኛውም ሰው፣
ሐ) የዋስትና መብት ማስታወቂያ ላስመዘገበ ማንኛውም ዋስትና ያለው ሌላ ገንዘብ ጠያቂ፣ እና
መ) ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን በይዞታው ሥር በሚያደርግበት ጊዜ መያዣው ቀደም ሲል በይዞታው ሥር ለነበረ ማንኛውም ዋስትና ያለው ሌላ ገንዘብ ጠያቂ፣
መስጠት አለበት፡፡
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የሚሰጥ ማስታወቂያ፣
ሀ) መያዣ ሰጪውን እና ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂን፣
ለ) የመያዣውን መግለጫ፣
ሐ) ወለድና ተገቢ የሆነ የማስከበሪያ ወጪ ግምትን ጨምሮ ዋስትናው የተጠበቀ ግዴታን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን፣
መ) የታቀደው ማስተላለፍ ስለሚፈጸምበት ሁኔታ፣
ሠ) ከመቼ ቀን በኋላ መያዣው እንደሚሸጥ፣ እንደሚተላለፍ፣ እንደሚከራይ ወይም ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ እንደሚሰጥ ወይም በሐራጅ የሚሸጥበትን ጊዜና ቦታ፣
መግለፅና ማመልከት አለበት፡፡
3/ ማስታወቂያው ይዘቱን በተገቢው ሁኔታ ይገልጻል ተብሎ በሚጠበቅ ቋንቋ መሆን አለበት፡፡ ሆኖም ለመያዣ ሰጪው የሚሰጠው ማስታወቂያ የዋስትና ስምምነቱ በተጻፈበት ቋንቋ ከሆነ በቂ ነው፡፡
4/ የማስታወቂያው ይዘት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተውን መረጃ ካካተተ በንዑስ አንቀጹ ከተመለከተው ውጭ የሆነ መረጃ ቢይዝም ወይም ከባድ ስህተት የማያስከትሉ አነስተኛ ግድፈቶች ቢኖሩትም በቂ ይሆናል፡፡
5/ ማስታወቂያ መስጠት የማያስፈልገው መያዣው፣
ሀ) ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ይዞታ ሥር ከሆነ በኋላ ያሉት አሥር የሥራ ቀናት ከማለቃቸው በፊት የሚበላሽ ከሆነ፣
ለ) ዋጋው በፍጥነት የሚወርድ ከሆነ፣
ሐ) በታወቀ ገበያ ላይ የሚሸጥ ዓይነት ከሆነ፣ ወይም
መ) ለእንክብካቤውና ለጥበቃው የሚያስፈልገው ወጪ ከዋጋው አንፃር እጅጉን የሚበልጥ ከሆነ ነው፡፡
84. ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከመያዣው መተላለፍ የሚገኝ ተያያዥ ገቢን ለማከፋፈል ስላለው መብት
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 82 መሠረት በሚደረግ የመያዣ ማስተላለፍ ሂደት የሚገኝ ተያያዥ ገቢን፡
ሀ) መያዣውን መልሶ ለመውሰድ፣ ለመያዝ፣ ለማስተላለፍ ዝግጁ ለማድረግ፣ ለማሻሻል እና ለማስተላለፍ ለሚወጣ ተገቢ ወጪ፣
ለ) መያዣውን ለማስተላለፉ መነሻ በሆነው የዋስትና መብት ላይ ያሉ ግዴታዎች ለመወጣት፣ እና
ሐ) የገቢው ክፍፍል ከመጠናቀቁ በፊት የበታች የሆነ የዋስትና መብት ወይም ሌላ ዋስትና ያለው ሰው ድርሻው እንዲሰጠውና ዋስትና የተገባላቸው ግዴታዎች እንዲፈጸሙ ጥያቄ ካቀረበ፡
በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ቅደም ተከተል መሠረት ክፍያውን ይፈጽማል፡፡
2/ የበታች የሆነ የዋስትና መብት ወይም ሌላ ዋስትና ያለው ሰው ስለጥቅሙ ወይም ስለዋስትና መብቱ ሌላ ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ከተጠየቀ ተገቢውን ማረጋገጫ ተገቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልተፈፀመ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) (ሐ) መሠረት የበታች የሆነ የዋስትና ባለመብቱ የሚያቀርብለትን ጥያቄ ለማክበር አይገደድም፡፡
3/ በተወዳዳሪ ባለመብቶች መካከል የመብት ወይም የቀዳሚነት ክርክር ሲነሳ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የፍርድ ቤት ወይም ሌላ ሥልጣን ያለው አካል ትዕዛዝን የያዘ ባለመብት እስከሚመጣ ድረስ ተራፊውን ገንዘብ ወለድ በሚያስገኝ ዝግ ሂሳብ ውስጥ እስከ ስልሳ ቀናት ለማስቀመጥና ሂሳቡንም ይዞ ለማቆየት ይችላል፡፡
4/ የዋስትና መብት በማስከበር የሚገኘው ገቢ ዋስትናው የተጠበቀ ግዴታን ለመወጣት ከዋለ በኋላ ላልተከፈለው ቀሪ ዕዳ ባለዕዳው ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
5/ መያዣ ሰጪው ለተረፈው ገቢ ባለመብት ይሆናል፡፡
85. ዋስትና ለተገባለት ግዴታ ሙሉ ወይም ከፊል የአፈጻጸም መያዣውን ስለመውሰድ
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ዋስትና ለተገባለት ግዴታ ሙሉ ወይም ከፊል አፈጻጸም ሲባል አንድ ወይም ከአንድ በላይ የዋስትና መያዣዎችን ለመውሰድ የጽሑፍ ምክረ ሐሳብ መያዣዎቹ ከመተላለፋቸው በፊት ወይም በሚተላለፉበት ጊዜ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ምክረ ሐሳቡን፣
ሀ) ለመያዣ ሰጪው፣
ለ) ዋስትና የተገባለት ግዴታ ከፊል አፈጻጸምን በሚመለከት ብቻ ከሆነ ለባለዕዳው፣
ሐ) ለመያዣ ሰጪው ከመላኩ ወይም መያዣ ሰጪው ምክረ ሐሳቡን ከመቀበሉ አሥር ቀናት አስቀድሞ በመያዣው ላይ ስላለው መብት በጽሑፍ ላሳወቀው ማንኛውም ሰው፣
መ) ለመያዣ ሰጪው ከመላኩ ወይም መያዣ ሰጪው ምክረ ሐሳቡን የመቀበል መብቱን ከመተዉ ከአሥር ቀናት አስቀድሞ መያዣውን አስመልክቶ ማስታወቂያ ላስመዘገበ ሌላ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣ እና
ሠ) መያዣውን በይዞታው ሥር ባደረገ ጊዜ መያዣው ቀደም ሲል በይዞታው ሥር ለነበረ ሌላ ማንኛውም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ፣
መላክ ይኖርበታል፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የቀረበ ምክረ ሐሳብ፣
ሀ) ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂንና የመያዣ ሰጪውን ማንነት፣
ለ) ማስታወቂያው በተላከበት ቀን ያልተከፈለውን ዕዳ ከነወለዱና ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መብቱን ለማስከበር ያወጣውን ወጪ እንዲሁም መያዣውን በመውሰድ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስፈልገውን መጠን፣
ሐ) ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ለግዴታው አፈጻጸም መያዣውን የሚወስደው በሙሉ ወይም በከፊል መሆኑን፣
መ) መያዣውን፣
ሠ) ባለዕዳው ወይም የመያዣ ሰጪው በአንቀጽ 79 መሠረት መያዣውን መልሶ ለመውሰድ ያለውን መብት፣ እና
ረ) ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ከመቼ ቀን በኋላ እንደሚወሰድ፣
ለይቶና በዝርዝር መግለፅ አለበት፡፡
4/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን የሚወስደው፣
ሀ) ዋስትናው ለተጠበቀ ግዴታ ሙሉ አፈጻጸም ከሆነ ማስታወቂያውን የመቀበል መብት ካለው ማንኛውም ሰው ማስታወቂያው በተላከለት አሥራ አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ የጽሑፍ ተቃውሞ ካልቀረበለት፣ እና
ለ) ዋስትናው ለተጠበቀ ግዴታ ከፊል አፈጻጸም ከሆነ እያንዳንዱ ማስታወቂያው የተላከለት ሰው ማስታወቂያው በተላከ በአሥራ አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ፈቃደኛነቱን በጽሑፍ ካረጋገጠ ብቻ፣ ነው፡፡
86. በመያዣው ላይ ስለሚገኝ መብት
1/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ከሸጠ ወይም ካስተላለፈ፣ ገዢው ወይም የተላለፈለት ሰው ከሺያጩ ወይም ከአስተላላፊው ሌላ ቀዳሚ የዋስትና መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከሌለ በስተቀር መያዣውን የማስያዝ መብት የሚያገኘው መያዣውን ከሸጠውና የበታች የሆነ ተወዳዳሪ የዋስትና መብት ነጻ በሆነ መንገድ ነው፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ መያዣውን ካከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ከሰጠ፣ ተከራዩ ወይም ፈቃዱ የተሰጠው ሌላ ቀዳሚ የዋስትና መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከሌለ በስተቀር ኪራዩ ወይም ፈቃዱ በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የሚያስገኘውን ጥቅም ያገኛል፡፡
3/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከዚህ ክፍል ድንጋጌዎች ውጭ መያዣውን ከሸጠ ወይም ካስተላለፈ፣ ካከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ከሰጠ ገዢው ወይም የተላለፈለት ሰው፣ ተከራዩ ወይም ባለፈቃዱ በመያዣው ላይ መብት ወይም ተጠቃሚነትን የሚያገኘው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የዚህን ክፍል ድንጋጌዎች በመጣስ መያዣ ሰጪውን ወይም የሌላን ሰው መብት ጉልህ በሆነ አኳኋን መጉዳቱን ካላወቀ ነው፡፡
87. ከተሰብሳቢ ሂሳብ፣ ከተላላፊ የገንዘብ ሰነድ፣ በተቀማጭ ሂሳብ ገቢ ከተደረገ ገንዘብ ወይም ከሴኩሪቲ ክፍያ ስለመሰብሰብ እና ስለመጠየቅ መብት
1/ ከግዴታ አለመወጣት በኋላ በተሰብሳቢ ሂሳብ፣ በተላላፊ የገንዘብ ሰነድ ወይም ሴኩሪቲ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከተሰብሳቢው ሂሳብ ባለዕዳ፣ ከተላላፊ የገንዘብ ሰነዱ ተገዳጅ ወይም ከሴኩሪቲ አውጪው ክፍያ መሰብሰብ ይችላል፡፡
2/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከግዴታ አለመወጣት አስቀድሞ የመያዣ ሰጪውን ፈቃድ ካገኘ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ክፍያ የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም ይችላል፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ወይም (2) መሠረት ክፍያ የመሰብሰብ መብቱን የሚያስፈጽም ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የክፍያ መያዣውን በሚደግፍ ወይም በሚያረጋግጥ ማንኛውም ግላዊ ወይም የንብረት መብት ላይም መብቱን ማስከበር ይችላል፡፡
4/ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1)-(3) መሠረት ክፍያ የመሰብሰብ መብቱን ከአንቀጽ 70 እስከ 74 በተደነገገው መሠረት ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡
5/ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ያለውን መብት በአንቀጽ 17 (2) መሠረት በቁጥጥር ስምምነት ተፈጻሚ ካደረገ ብቻ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተቀማጭ ገንዘብ የመቀበል መብት ካላቸው የፋይናንስ ተቋማት ክፍያ መሰብሰብ ይችላል፡፡
88. የተሰብሳቢ ሂሳብ መብት ሙሉ በሙሉ የተላለፈለት ሰው ስለሚሰበሰበው ክፍያ
የተሰብሳቢ ሂሳብ መብት ሙሉ በሙሉ የተላለፈለት ሰው ክፍያውን አስተላላፊው ግዴታውን ከመወጣቱ በፊት ወይም በኋላ መሰብሰብ ይችላል፡፡

ክፍል ስምንት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

89. ከቴምብር ቀረጥ ነፃ መሆን
በዚህ አዋጅ መሠረት የዋስትና መብትን ለመመሥረት የሚደረግ ስምምነት ወይም ግብይት ከቴምብር ቀረጥ ክፍያ ነፃ ነው፡፡
90. ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በተጀመሩ ክርክሮች ላይ ተፈፃሚ አለመሆኑ
1/ ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት የተጀመረ የፍርድ ቤት ወይም የሽምግልና ጉባዔ ክርክር ላይ ቀደምት ሕግ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
2/ ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት የተጀመረ ቀደምት የዋስትና መብት አፈጻጸም በቀደምት ሕግ መሠረት ሊቀጥል ይችላል፡፡
91. መብትና ግዴታዎችን ስለማስተላለፍ
1/ በሌሎች ሥራ ላይ ባሉ ሕጐችና ድንጋጌዎች መሠረት፣
ሀ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሽከርካሪዎች፣
ለ) የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች፣ እና
ሐ) የንግድ ሚኒስቴር በንግድ ተቋማትና በዱቤ ግዥ ውል፣
በተንቀሳቃሽ ንብረት፣ የዋስትና መብት ምዝገባ ጋር በተገናኘ ያሏቸው መብቶችና ግዴታዎች በዚህ አዋጅ መሠረት ለመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተላልፈዋል፡፡
2/ ማንኛውም ሌላ መንግሥታዊ ተቋም በሌሎች ሥራ ላይ ባሉ ሕጐች ድንጋጌዎች መሠረት የሌሎች ግዑዝ እና ግዑዝነት የሌላቸው ተንቀሳቃሽ ሀብቶች የዋስትና መብት ምዝገባ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ያለው መብትና ግዴታ በዚህ አዋጅ ለመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተላልፏል፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ግዑዝ እና ግዑዝነት ለሌለው ሀብት የባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ባለቤትነቱን ከማስተላለፋቸው በፊት መብቱ ከዋስትና ነፃ መሆኑን ከዋስትና መዝገብ ማጣራትና ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
92. ቀደምት የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ስላለው ተፈፃሚነት
1/ በቀደምት ሕግ መሠረት በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ የነበረ የዋስትና መብት ከዚህ በታች ከተገለጹት አንደኛው በቅድሚያ እስከሚከሰት ድረስ በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ ሆኖ ይቀጥላል፤
ሀ) በቀደምት ሕግ መሠረት በሦስተኛ ወገን ላይ ያለው ተፈፃሚነት ይህ አዋጅ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ባሉት አስራ ሁለት ወራት ጊዜ ማብቃት፣ ወይም
ለ) ይህ አዋጅ ከፀና በኋላ ባሉት አሥራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የዋስትና መብቱን በመያዣ መዝገቡ የተመዘገበ እንደሆነ ነው፡፡
2/ ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በመያዣ ሰጪው እና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል ቀደምት የዋስትና መብት ለመመስረት በጽሑፍ የተደረገ ስምምነት መያዣ ሰጪው ይህ አዋጅ ከፀና በኋላ ማስታወቂያው እንዲመዘገብ ፈቃደኛነት ያለው መሆኑን ለማሳወቅ በቂ ነው፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ቀደምት የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ያለው ተፈፃሚነት ከማብቃቱ በፊት የዚህ አዋጅ በሦስተኛ ወገን ላይ ያለው ተፈፃሚነት ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በዚህ አዋጅ መሠረት ቀደምት የዋስትና መብቱ በቀደምት ሕግ መሠረት በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ተፈፃሚ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ቀደምት የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ያለው ተፈፃሚነት ከማብቃቱ በፊት የዚህ አዋጅ የሦስተኛ ወገን ተፈፃሚነት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ቀደምት የዋስትና መብቱ በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ የሚሆነው በዚህ አዋጅ መሠረት በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
93. የተሻሩና ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ሕጐች
1/ በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት በወጣ አዋጅ ቁጥር 97/1990 ውስጥ በተንቀሳቃሽ ንብረት የመያዣ መብት ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ድንጋጌዎች በሙሉ በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፡፡
2/ ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ ቁጥር 98/1990 በዚህ አዋጅ ተሽሯል፡፡
3/ ይህን አዋጅ የሚቃረን ማንኛውም ህግ፣ደንብ፣መመሪያ ወይም ልማዳዊ አሰራር በዚህ አዋጅ የተሸፈኑ ጉዳዮችን በሚመለከት ተፈፃሚነት አይኖረውም
94. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
1/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልግ ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡
2/ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ይህን አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት የወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል፡፡
95. የመሸጋገሪያ ድንጋጌ
ራሱን የቻለ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በደንብ እስኪቋቋም ድረስ፣ የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤትን ለማደራጀት፤ የመያዣ መዝገብ ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ ስራ ለማስጀመር፣ እና ሬጅስትራሩን ለመሾም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
96. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፤ ሆኖም የመያዣ መዝገቡ ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

አዲስ አበባ ቀን ___________2011 ዓ.ም.

ሣህለወርቅ ዘውዴ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት