ሃዋ ሙሐመድ፣ እናቴዋ!
(ከጉዞ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
ከደሴ ወደ ራያ ቆቦ በሚኒባስ ተሳፍሬ እየተጓዝኩ ነው። ወደ ትውልድ ቀየየ ከረዥም ጊዜ በኋላ ለሃዘን ስለነበር የምሄደው በመስኮቱ ወደ ውጭ እየተመለከትኩ በውስጤ ብዙ ነገር እያሰላሰልኩ (ባርባር እያለኝ) ከአጠገቤ የተቀመጡ ጉፍታ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉ ደርባባ ሁለት ሙስሊም እናቶች የሚያወሩትን ልብ ብየ አልሰማቸውም ነበር። አንዷ እናት ለምታወራው ነገር ማዋዣ ይሆን ዘንድ “የምን ነገር ማንዛዛት ነው፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ሲባል ሰምተሽ አታውቂም” ስትል ድንገት ሰማኋት። የህግ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ የማስረጃ ህግ ትምህርት ውስጥ በወንጀል ጉዳይ የአንድን ማስረጃ በተለይም የእምነት ቃል ቅቡልነት(admissibility) የሚወስነው ሂደቱ(the means justifies the end) ወይስ ውጤቱ (the end justifies the means)የሚል የጦፈ ክርክር እናደርግ ነበር። የኋላኛውን ሃሳብ የምናቀነቅን ተማሪዎች የአንድ የማስረጃ ውጤት ፍትህ ላይ የሚያደርስ ከሆነ እንዴት ተገኘ የሚለው ሥነ ስርዓታዊ ሂደቱ አያሳስብም። ሂደቱ ችግር አለበት ብለህ ማስረጃውን ውድቅ ከምታደርግ ይልቅ በሂደቱ ላይ ህገወጥ ድርጊቱን የፈፀመውን መርማሪ በወንጀልና በፍትሃብሄር ተጠያቂ በማድረግ ወደፊት ተመሳስይ ድርጊት እንዳይፈፀም መቀጣጫ ማድረግ ይገባል እንላለን። ለዚህ መከራከሪያ ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው እያልን ክርክራችንን በምሳሌያዊ አባባል እናጅባለን። አሁንም ቀጥሏል፣ ግን አቋሜን ቀይሪያለሁ። ሆኖም ግን ስለዚህ ምሳሌያዊ አባባል አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ ሰምቼ አላውቅም ነበር። ታዲያ እኔም ከቁዘማየ ነቅቼ በወጋቸው መሃል ጣልቃ ስለገባሁ ይቅርታ ጠይቄ (የኛ ሰው ወግ አደናቃፊን “ምን እንደ እርጎ ዝምብ ጥልቅ ትላለህ ብሎ ይገስፃል፣ እስኪ ልጨርስ አድምጥ ሲልህ ነው) ጥያቄን አቀረብኩ “ይህ አባባል ለምን ተባለ፣ መነሻው ምንድነው ብየ ጠየኩ?”። ዝምታ ሆነ። ተያየን። አንዷ እናት ዝምታውን እንድህ ስትል ሰበረችው። ድሮ ነው አሉ። አንዲት የባርያ አሳዳሪ ባርያዋን ሁለት ቁና ጤፍ እንድትፈጭላት ጤፉን ከጎተራው ስፍራ ሰጥታት ወደ ጓዳ ተመለሰች። ባርያዋም በስራ ጫና በጣም ደክሟት ስለነበር የወፍጮውን መጅ መግፋት ተስኗት “እመቤቴ ማርያም አንቺው ያረግሽ አርጊው” ብላ እተማጠነች እያለ እንቅልፍ ሸለብ አረጋት። ከእንቅልፏ ስትነቃ ቁናው በዱቄት ተሞልቶ አገኘችውጭ። ደነገጠች፣ ጦለቴ ደርሶ ነው ብላ አመነች። ዱቄቱን ለአሳዳሪዋ አስረከበች ሆኖም ግን አሳዳሪዋ በዚህ ፍጥነት እንዴት ይሄን ልትፈጭ ቻልሽ? እንደውም የወፍጮውን ድምፅ አልሰማሁም? ይሄን ዱቄት አልቀበልም ጤፌን መልሽ አለቻት። ባርያዋም ግራ ገባት እንዳትመልስ ምንም የላት፣ ቢጨንቃት ዳኛ ይፍረደን አለች። ይፍረንደን፣ አለች መልሳ አሳዳሪዋ። ተያይዘው ወደ አጥቢያ ዳኛ ሆዱ። ጉዳዩን አስረዱ። የአጥቢያ ዳኛው የአሳዳሪዋን የክርክር ሃሳብ በመደገፍ የሾይጣን ስራ ካልሆነ በስተቀረ ወፍጮ ሲፈጭ ድምፅ ሳያወጣ እህል አይፈጭም ስለዚህ ሁለት ቁና ጤፉን መልሽ ብሎ ፈረደ። መቼስ የፍርድ ባለእዳ መሆን አስጨናቂ ነውና አውጥታ አውርዳ “እረኛ ይፍረድን” ብላ ተማፀነች። ምን ገዶኝ አለች አሳዳሪዋ። ለእረኛው ዝርዝሩ ተነገረው የራሱን ፍርድ እንዲህ ሲል ገለፀው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው”። “ዋናው ሁለት ቁናው ጤፍ ሳይጎል መፈጨቱ እንጂ በማን፣ እንዴት እና የት ተፈጨ የሚለው አያሳስብም ብሎ ድሃዋን ከጭንቀት ታደጋት ” ይባላል፣ ገምሻራየዋ ታሪኩ ይኽው ነው። በቅንነት የተሞላው የትረካቸው ለዛ ሃዘኔን አስረሳኝ። ሙስሊም ሆነው ሳለ የዘመኑ የእኛና እነሱ ትርክት ሰለባ ሳይሆኑ በቅንነት የእመቤቴ ማርያምን ስም እየጠቀሱ ተአምረ ማርያምን (እንደማንበብ ያህል) ተረኩልኝ። ይህ አልገረመኝም ምክንያቱም ወሎ እንዲህ ነው። የሚጠቅመውን የራሱ ያደርገዋል። የገሌነው ብሎ ጎራ አይለይም፤ አያከርም። ክርስቲያኑም እንደዛው። ብዙ ክርስቲያኖች ጀማ ንጉስ ለመውሊድ ሄደው ዱኣ እስደርገው ሲመለሱ አይቻለሁ፣ እኔም ኑሬበታለሁ። ይህ ለዘመናት የዳበረ የሕይዎት ዘይቤ ነው እንዲህ በዋዛ የማይፈታ።
ወጋችንን ቀጠልን። ትንሽ አሰብኩና፣ ይህን አባባል አላምንበትም። ድሃዋን እናት ከጭንቅ ቢገላግላትም በውስጡ ብዙ ችግር አለበት። በዚህ ዘመን ልንጠቀምበት አይገባም አልኳቸው። “መቼም የዘመኑ ልጆች ጉዳችሁ አያልቅም” ብለው ትክ ብለው ተመለከቱኝ፣ እስኪ ተናገር እንስማህ መሆኑ ነው። ስንፍናን፣ ሌብነትንና ህገወጥ አሰራርን ወ.ዘ.ተረፈ እንዲንሰራፋ ያበረታታል። በዚህም እንደጉዳዩ ሁኔታ ግለሰቦች፣ ሃገር፣ መንግስትና ህዝብ ይጎዳል። ወደፊት እንዳይራመዱ ገድቦ ይይዛል። አለፍ ሲልም ሃገር ያፈርሳል፣ ጠባቂ መከታ መንግስት እንዳይኖር ያደርጋል። ሰው ያለውን ጉልበት፣ እውቀት፣ ጊዜውንና ገንዘቡን አቀናጅቶ እንዳይሰራ ያደርገዋል፤ በአቋራጭ መበልፀግን ይመኛል። ትላንት እዚህ ግባ የማይባል ገቢ የነበረው ድንገት የናጠጠ ቱጃር ሲሆን ከየት፣ እንዴት እና መቼ ይህን ንብረት አፈራው ተብሎ ላይጠየቅ ነው? የወንጀል ፍሬ ቢሆንስ? በሌላ በኩል ለፍቶ ደክሞ በላቡ ሳያመርት፣ ሳይሰራ የሌሎችን እንዲያማትር ያደርጋል። ያሰንፋል፣ ክፉ በሽታ ነው። የመንግስት አካላትም በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት መወጣት ያለባቸው በህግ የተደነገጉ የአሰራር ሥርዓቶችን አክብረው መሆን ይገባቸዋል። የግብር ይውጣ አሰራር በጊዜ ሂደት ተጠያቂነት ያስቀራል፣ ስርዓት ያፈርሳል። ለአብነት ያህል ፓሊስ የወንጀል ተጠርጣሪ ሲያስር ወይም ቃል ሲቀበል በሥነ ስርዓት ህጉ የተቀመጡ የተከሳሽ መብቶችን ባከበረ መልኩ መሆን ይገባዋል። ተጠርጣሪውን መደብደብ፣ ማሰቃየትና ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ነገር መፈፀም የለበትም። ከድብደባው ስቃይ ለማምለጥ ሲል ያልፈፀመውን ወንጀል ፈፅሜያለው ቢልስ? ንፁህ ሰው ወንጀለኛ አድርገን ትክክለኛ ወንጀል ፈፃሚዎችን ነፃ ልናደርግ አይደለም ወይ? በድብደባው ምክንያት ሕይወቱን ቢያጣ ወይም በአካሉ ላይ ቋሚና ግዚያዊ ጉዳት ቢደርስበትስ? ለዚህ ችግር ማን ነው ተጠያቂው? ዜጎች በፍትህ ተቋሞቻችን ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይህ ሁሉ ተጠረቃቅሞ ሃገር በህግ የበላይነት ሳይሆን በሰዎች የበላይነት እንድትመራ ያደርጋል። የወገን አለኝታ የሆኑ ተቋሞች እንዳይኖሩን ያደርጋል። መዘዙ ብዙ ነው። እናቶቼ ስሙኝማ…የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው አይበጀንም ይቅርብን አልኳቸው። አንደኛዋ እናት፣ “እኛ ይህን ሁሉ ጉድ መች አወቅንና እንደው ዝም ብለን አፋችን ያመጣልንን እናወራለን እንጁ…” እያሉ ..መኪናው ቆመ.. ረዳቱ… መርሳ ወራጅ ሲል.. ሁለቱ እናቶች ለመውረድ እቃቸውን እየሰበሰቡ….”ገምሻራየዋ” በል በደህና ግባ፣ መንገዱ ቀና ይሁንልህ፣ ቤተሰቦችህን በኸይር አግኛቸው ብለው መርቀው..ተሰናብተውኝ ወረዱ። መኪናው ሳይንቀሳቀስ በፊት ድምፄን ከፍ አድርጌ..ማዘር… ስመዎን አልነገሩኝም እኔ ኃይለማርያም እባላለሁ የአንቱስ?…መከናው ተንቀሳቀሰ..”ሃዋ መሃመድ” የሚል ድምፅ ጆሮየ ላይ ደረሰ።
ሃዋ ኑልኝ፣ እድሜዎ ይርዘም አቦ። አሜን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s