የፖለቲካ ገለልተኝነት ዐቃቤ ሕግ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም

በዘሪሁን ሽፈራው
e-mail: zerihunshiferaw490@gmail.com

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፷፪/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፷፫ የፖለቲካ ፓርቲ ስለ መመስረት ያትታል፡፡
ይህ አንቀጽ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት መኖሩን እንዲሁም ማንኛውም እድሜው ከ፲፰ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት የአገር አቀፍ ወይም የክልል የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት እንዳለው ያስረዳል፡፡
ይህ ጠቅላላ ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጉ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ክልከላ ያስቀመጠባቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በዚህ ዝርዝር የሚገኙ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባል፣ የፖሊስ፣ የደህንነት እና የጸጥታ አካላት ሰራተኛ እና የምርጫ ቦርዱ ባለስልጣናት እና ሰራተኞች ናቸው፡፡
ሁለት ወዶ አይቻልምና እነኝህ ሥራችሁን ብቻ ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ግዴታ የተጣለባቸው ሰዎች በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመንቀሳቀስ ከፈለጉ የመንግሥት ስራቸውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ይህ ሀሳብ በግልጽ በአዋጁ አንቀጽ አንቀጽ ፷፫(፬) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ገደቡን በማለፍ ሥራዉን ሳይለቅ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ያለመሆን ድንጋጌውን በመጣስ በፖለቲካ የሚሳተፊ ግለሰብ ከያዘው የመንግሥት ሥራ በራሱ ፈቃድ እንደለቀቀ ተቆጥሮ በሚመለከተው አካል አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል፡፡
በዚህ ምርጫ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያለመሆን ግዴታ ከተጣለባቸው ሥራ ዘርፎች የዐቃቤ ሕግ ሥራን በተመለከተ ከዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ ሕጎች እና መተዳደሪያ ደንቦች አንጻር በመመርመር መሠረታዊ የሕግ አተረጓገም መርህ አንጻር ሁሉም ዐቃቤ ሕግ ከፖለቲካ አባልነት ነጻ የመሆን ግዴታ አለበት ወይስ አይደለም በሚለው ክርክር ልያስነሳ በሚችል ሀሳብ ላይ የሚከተለው መደምደሚያ መስጠት ይቻላል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፱፻፵፫/፪ሺ፰ ዓ.ም አንቀጽ ፪ (፰) “ዓቃቤ ሕግ” ማለት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተሹሞ በዓቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የሚተዳደር የሕግ ባለሙያ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፯ (፩) መሠረት የተሾሙ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንና ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤያነ ሕግን ይጨምራል በማለት ትጉም ይሰጣል፡፡ ይህንን ትርጉም እስከ ሥር መዋቅር ባሉ ኃላፊዎች በማዳረስ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር ፻፸፯/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፪(፲፪) “ዓቃቤ ሕግ” ማለት በመስተዳድር ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት የሚቀጠር ወይም የሚመደብ እና የሚተዳደር የሕግ ባለሙያ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፯ መሠረት የተሾሙ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን፣ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤያነ ሕግን እና በየእርከኑ ያሉት የዓቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችንም ይጨምራል በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ዐቃብያነ-ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር ፻፸/፪ሺ፲፩ ዓ.ም አንቀጽ ፷፪ ስለ ዐቃቤ ሕግ ገለልተኝነት ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ማንኛዉም ዐቃቤ ህግ በፖለቲካ እንቅስቃሰ መሳተፍ ወይም አባል መሆን ወይም አመለካከቱን በስራ ላይ መግለፅ ወይም በማናቸዉም መንገድ ማሳየት የተከለከለ ነዉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፪(፪) የተሰጠው የዐቃቤ ሕግ ትርጉም የተቋሙ ኃላፊዎችንና ምክትሎችን እንዲሁም በየደረጃው እስከ ሥር መዋቅር የሚመዘረጋውን ካላይ ካየናቸው ሕጎች በተለየ መልኩ ነው የሚተረጉመው፡፡ ይህ ደንብ “ዓቃቤ-ሕግ” ማለት በዚህ ደንብ አንቀጽ ፮ ከተመለከተው የስራ ደረጃ ዝርዝር በአንዱ የተቀጠረ ወይም የተመደበ ሰው ነው በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡ ዝርዝሩ የሚያካትተው ከተቋሙ ኃላፊና ምክትሎች ውጭ ያሉትን ዐቃቤ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ካየናቸዉ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ፣ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጆች እና ዐቃብያነ-ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ስለዐቃቤ ሕግ የተደነገጉ ሀሳቦችን ስንመለከት የምርጫ አዋጁ ያስቀመጠው ክልከላ መተግበር ያለባቸዉ የትኛው ዐቃቤ ሕግ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመሥጠት የዐቃቤ ሕግ ትርጉም ስንፈልግ የዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እና መተዳደሪያ ደንብ የተለያየ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ በሕግ ተዋረድ/hierarchy of law/ ደንብ ከአዋጅ ዝቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ደንብ አዋጅ በጥቅል የሚያስቀመጣቸዉን ሀሳብ በዝርዝር በማብራራት ለአፈጻጸም እንዲመች ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ የሰጣቸዉን መብት የማጣበብ እንዲሁም ትርጉም መቀነስ አቅም አይኖረዉም፡፡ ከዚህ መርህ አንጻር ከላይ ባየነዉ ደንብ ለዐቃቤ ሕግ የተሰጠው ትርጉም ከአዋጁ የሚጻረር በመሆኑ የደንቡ ትጉም ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ ማለት በትክለኛ የሕግ አተረጓገም ሥርዓት ከፖለትካ ወገንተኝነት ነጻ የመሆን ግዴታ የዐቃቤ ሕግ ባለሙያዎች እና የተቋሙ መሪዎች ጭምር ነው ማለት ነው፡፡
ማን ያውቃል የተቋሙ ኃላፊ መሆን የሚገባው የፖለቲካ ተሿሚ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ ተቋም አንዱ የአስፈጻሚ ተቋም ነው ስለዚህ ይህንን ተቋም መምራት ያለበት በፖለቲካ ታማኝነት ያለው የገዥ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው መሆን አለበት የሚል አቋም ያላቸዉ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ከላይ ላስቀመጥኩት መደሚደሚያ መነሻ ያረኩት እነኝህን ምክንያቶች ሳይሆን የሕግ አተረጓገም መርህ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡
ከዚህም ባሻገር ዐቃቤ ሕግ ተቋም ከአስፈጻሚ ተቋማት ውጭ የሆነ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም ተደርጎ የሚጣይባቸዉ ሀገራት እንዳሉ በሀገራችንም በደርግ ዘመን ልዩ ዐቃቤ ሕግ በሚል ከሌሎች አስፈጻሚ ተቋማት በተለየ መልኩ ተዋቅሮ እንደነበረ የሚያሳዩት ዐቃቤ ሕግ ተቋም ከሌሎች አስፈጻሚዎች ለይተዉ ከፖለቲካ ገለልተኛ በሆነ መልኩ ማዋቀር እንደሚቻል ማሳያ ልሆን ይችላል፡፡ የፍትህ ተቋማት ከሚባሉት አንጋፋዉ ፍርድ ቤት ከፖለትካ ገለልተኛ በሆነ ዳኛ/ፕረዚዳንት/ መመራቱ በማሕበረሰቡ ዘንድ ለፍትህ ያለውን አመለካከት ከፍ ማድረጉ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ የዚህንም አምሳል /analogy/ ለዐቃቤ ሕግ ተቋም መጠቀም ይቻላል፡፡
በመሆኑም የሕዝብ ተአማኒነት ያለው፣ በተሟላ ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነት የሚያገለግል እንዲሁም ለሙያዊ፣ ተቋማዊና ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሚገዛ፣ በግልጽነትና አሳታፊነት የሚሰራ የዓቃቤ ሕግ ተቋም የማደራጀት ዐላማ ይዞ በተቋቋመዉ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ዐላማዉን ወደ ግብ ለማድረስ ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የተቋሙ መሪዎቹንም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሚያደርግ አሠራር ልኖር እንደሚገባ እንዲሁም በአዋጅ የተሰጠዉን ትርጉም ደንብ ዋጋ ማሳጣት ስለማይችል የአዋጁን ትርጉም በመተግበር ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የተቋሙ ኃላፊዎችንም ገለልተኛ በማድረግ ለፍትህ የቆሜ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም እዉን መደረግ አለበት እላለሁ፡፡78850670_2519381988350688_6360868684457574400_o

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s